ወሎ ዩኒቨርሲቲ ለሆስፒታሎች የመድሃኒት ድጋፍ አደረገ

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ለቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል እና ለደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመድሃኒት ድጋፍ አደረገ።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፉ ለደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 12 ካርቶን እና ለቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ደግሞ 6 ካርቶን መድሃኒት ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉንም የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር እንድሪስ መሀመድ እና የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ተበጀ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ጉግሳ በኩል ተረክበዋል።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረገ ነው ያሉት የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ተበጀ ለተደረገላቸው የመድሃኒት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ከወረቀት ንክኪ ነጻ የሆነ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት በሚያደርገው ሽግግር የወሎ ዩኒቨርሲቲ ሚና ትልቅ ድርሻ አለው። ሆስፒታሉ ለሚያደርገው የዲጅታላዜሽን እንቅስቃሴ ዩኒቨርሲቲው ኃላፊነት ወስዶ 80% ስራውን አጠናቋል ብለዋል።

የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመምጣቱ እና አፋርን ጨምሮ ለምስራቅ አማራ ለቆዳ፣ ለዓይን፣ ለአባላዘር እና ለስነ ዓዕምሮ ህክምና የሪፈራል ማዕከል ነው። በመሆኑም በስፔሻሊስት ሀኪሞች እና በማቴሪያል የወሎ ዩኒቨርሲቲን ቀጥይነት ያለው ድጋፍ እንፈልጋለን ሲሉ አቶ ሲሳይ ገልጸዋል።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሰሜኑ ጦርነት ለተጎዱ ሆስፒታሎች ውጭ ሀገር ካሉ ለጋሽ ድርጅቶችና ተቋማት የህክምና ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ መሆኑ የሚታወስ ነው።

Scroll to Top