ወሎ ዩኒቨርሲቲ ለደሴ ከተማ የመቄዶንያ ማዕከል እና በአካባቢው ለሚገኙ የተፈናቃይ ካምፖች ድጋፍ አደረገ
ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሚያከናውነው የማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ለደሴ ከተማ መቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል እና በአካባቢው ለሚገኙ የተፈናቃይ ካምፖች የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል። ከዚሁ ስራው ጋር በተገናኘ የማህበረሰብ አገልግሎት ኃላፊነቱን ለመወጣትና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለማገዝ ለደሴ ከተማ መቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል 20 ኩንታል ነጭ ዱቄት፣ 50 ፍራሽ፣ 24 ጠርሙስ የፀጉር ቅባት፣ 144 የአዋቂ ዳይፐር፣ 50 ነጠላ ጫማ፣ 3 ጥቅል አቡጄዲ እና 1080 ፓራሲታሞል ድጋፍ አድርጓል።
የደሴ ከተማ መቄዶንያ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዮሴፍ ለማ እና በማዕከሉ የሚኖሩት አረጋውያን ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ጊዜያት ለማዕከሉ ለሚያደርግላቸው ሙያዊና ቁሳዊ ድጋፍ አመስግነዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦች የተቋሙን ዓላማ በመረዳት ድጋፍ እንዳያደርጉላቸውም ጥሪ አድርገዋል።
ከዚሁ ድጋፍ ጋር በተያያዘ ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል በቃሉ ወረዳ ደጋን ከተማና ኩታበር ወረዳ በቻይና መጠለያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች 42 ኩንታል ነጭ ዱቄትና 3 ኩንታል ምጥን ሽሮ ድጋፍ አድርጓል። በተመሳሳይ የተፈናቃይ ካምፖቹ አስተባባሪዎችና በመጠለያ ካምፖቹ የሚኖሩት ተፈናቃዮች ዩኒቨርሲቲው በየጊዜው ለሚያደርግላቸው ድጋፍ አመስግነው ሌሎች አካላትም ያሉበትን ሁኔታ በመረዳት ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።
የተደረጉትን ድጋፎች በቦታው ላይ ተገኝተው ያስረከቡት የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ጉግሳ ናቸው።








