ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓም (ወዩ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጽ/ቤት)
ወሎ ዪኒቨርሲቲ ካናዳ አገር ከሚገኘው ግሎባል ኤይድ ኢትዮጵያና ፕሮጀክት ኪዩር ጋር በመተባበር ለደላንታ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የተለያዩ የህክምና መገልገያ እቃዎችን ድጋፍ አድርጓል። እቃዎቹ የቀዶ ህክምና መስሪያ፣ የህክምና አልጋዎች ከነፍራሻቸው፣ ኦክስጅን ኮንሰንትሬትር፣ የአልትራሳውንድ ማሽን፣ ስቴትስኮፕን ጨምሮ 120 የሚደርሱ የተለያዩ የህክምና መገልገያዎች ናቸው፡፡
በርክክቡ ስነስርዓት ላይ የተገኙት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ እንደተናገሩት ጦርነቱ ቁሳዊ ኪሳራና፣ ሰብዓዊና መንፈሳዊ ጠባሳ ከማድረሱም በላይ ከውድመቱ በመነሳት ከችግሩ ለማገገምም ሆነ ለመቋቋም ብሎም ወደተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ለኮን፣ ለቦሩ ሜዳ ፣ ለደሴ እና ለቆቦ ሆስፒታሎች የህክምና እቃዎች ከዚህ ቀደም ድጋፍ መደረጉን አሳውቀዋል፡፡ አስከትለውም ለደላንታ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የተደረገው ድጋፍ የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
ዶ/ር መንገሻ አያይዘውም በጦርነት የወደሙ ሆስፒታሎችን ለማቋቋም በውጭ አገር በፕሮጀክት የተገኘውን ድጋፍ ለማጓጓዝ በተለይም አቶ አሳየ እጅጉና ጓደኞቹ እንዲሁም ለሁሉም ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበው የመጡ የህክምና ቁሳቁሶች ሆስፒታሉን ወደላቀ ደረጃ ሊያደርሱ የሚችሉ በመሆናቸው ለተገቢው አላማና አገልግሎት እንዲውሉም አሳስበዋል። ከዚህም በተጨማሪ የደላንታ ሆስፒታልን ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግና አገልግሎቱን ለማሻሻል በሆስፒታሉ ካሉ ሰራኞች ውስጥ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል የሚያገኙበትን አጋጣሚ በመፍጠርና ሆስፒታሉን የTTP (team training program) ማዕከል በማድረግ የወሎ ዩኒቨርሲቲ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መታደል አዳነ በበኩላቸው ወሎ ዩኒቨርሲቲም በጦርነቱ የዘረፋና የውድመት ሰለባ ከመሆኑ አንጻር ሌሎችን ተቋሞች እና ሆስፒታሎች ለማቋቋም ሙሉ አቅም ባይኖረውም ነገር ግን የደላንታ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በነበረው ጦርነት የከፋና ከፍተኛ ውድመት የደረስበት መሆኑን በመገንዘብ በተወሰነ መልኩ ሆስፒታሉን ስራ ለማስጀመርና አጋርነታችንን ለመግለጽ የተደረገ ድጋፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ሆስፒታሉን በሙሉ አቅሙ ስራ ለማስጀመርና የአካባቢውን የጤና ችግር መፍታት ይቻል ዘንድ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ዲኑ በቀጣይም ከህክምና እቃዎች ድጋፍ ባለፈ በተለያዩ የህክምና ዘርፎች ሲኒየር ሃኪሞችን በመላክ ዩኒቨርሲቲው ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፋሪስ ኃይሉ በበኩላቸው እንዲህ አይነቱን ፈታኝ ጊዜ በጋራ ሆነን፣ ተጋግዘንና ተረዳድተን አንድ ሆነን ከሰራን እንወጣዋለን፡፡ ነገር ግን ሁሉም በየተሰማራበት የችግሩን አሳሳቢነት በውል በመረዳት መስራት ይጠበቃል ሲሉ አሳስበዋል።
የደላንታ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራአስኪያጅ ዶ/ር ጌታቸው አሰፋና የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ግርማ ታደሰ በበኩላቸው ወሎ ዩኒቨርሲቲና ግሎባል ኤይድ ከኢትዮጵያና ሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን የህዝብ ችግርን ለመቅርፍ የሚያደርጉትን እገዛ አድንቀው ለተደረገላቸው ድጋፍ በሆስፒታሉና በወረዳው ህዝብ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሜዲካል ዳይሬክተሩና ስራ አስኪያጁ አያይዘውም ሆስፒታሉ ከዘረፋና ውድመቱ ባሻገር ከሚያስተናግደው ከፍተኛ የህሙማን ቁጥር አንጻርና እንደ አዲስ ስራ ጀማሪ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዘርፈ ብዙ ጉድለቶች እንዳሉበት ጠቁመው ሌሎችም መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ግለስቦች ክፍተቱን በመለየት ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በመጨረሻም የደላንታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪና የሆስፒታሉ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ፈንታነሽ ታመነ ለሆስፒታሉ ለተደረገው ድጋፍ በወረዳው ህዝብ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።