የወሎ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና ትምህርት ቤት ዓለም አቀፍ የፈረሶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በኩታበር ወረዳ ለጋማ እንሰሳት የህክምና አገልግሎት ሰጥቷል።
በየአመቱ መጋቢት 1 የፈረሶችን ጤንነት፣ አመጋገብ እና አያያዝ ለማሻሻል ዓለም አቀፍ የፈረሶች ቀን ይከበራል። ይህንኑ ቀን ምክንያት በማድረግ የወሎ ዩኒቨርሲቲ የእንሰሳት ህክምና ት/ቤት በኩታበር ከተማ “Honoring Ethiopian Horses as Symbols of Victory and Economic Vitality” በሚል መሪ ቃል ለእንስሳቱ የህክምና አገልግሎት በመስጠት እለቱን አክብሯል። የእንሰሳት ህክምና ት/ቤት ዲን ዶ/ር አህመድ ያሲን ፈረሶች በአለም አቀፍ ደረጃ የድል እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ምልክቶች በመሆናቸው በዚሁ ቀን ከጥንት ጀምሮ ለሰው ልጅ የነበራቸው ግልጋሎት ሊታወስ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የእንሰሳቶችን ጤንነት በመጠበቅ አርሶ አደሮች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የእንሰሳቶችን ጤንነት እንዴት መጠበቅ፣ መመገብ እና መጠለያቸውን በምን መልኩ ማዘጋጀት እንዳለባቸው የግንዛቤ ፈጠራ ተሰጥቷል። በፕሮግራሙ የተገኙት የኩታበር ከተማና አካባቢው ማህበረሰብ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ለእንስሳቱ ላደረገላቸው ነጻ የህክምና አገልግሎት ምስጋና አቅርበዋል። የእንሰሳቶች ጤንነት እየተቃወሰ ያለው አንዱ ምክንያት ከአካባቢው ወደ ወንዙ በሚለቀቅ ፈሳሽ እና ደረቅ ቆሻሻ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ክትትል እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።
በዚህ ዓለም አቀፍ የፈረሶች ቀን የህክምና አገልግሎት የወሎ ዩኒቨርሲቲ የእንሰሳት ህክምና ትምህርት ቤት መምህራን፣ ረዳት ባለሙያዎችና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።


