ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ .ም ( ወሎ ዩኒቨርሲቲ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጽ/ቤት)
ወሎ ዩኒቨርሲቲ በ2015 ዓ.ም በደቡብ ወሎ፣ በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞንና በደሴ ከተማ ከ1ሺ 5 መቶ ሄክታር መሬት በላይ በበጋ የመስኖ ስንዴ እንዲሸፈን መደረጉን ተከትሎ በዛሬው እለት የደላንታ ወረዳ 200 ሄክታር የሚሸፍን የበጋ መስኖ ስንዴ ጉብኝት ተካሂዷል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ በጉብኝቱ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ዩኒቨርሲቲያችን እንደሃገር የተያዘውን የመስኖ ስንዴ ልማት ተግባራዊ ለማድረግ ከአካባቢው አስተዳደሮች (ከደቡብ ወሎ አስተዳደር፣ ከኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደርና ከደሴ ከተማ አስተዳደር ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዶ/ር መንገሻ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ለማህበርሰቡ የባለሙያ ስልጠና፣ የምርጥ ዘር፣ የማሽነሪ፣ የማዳበሪያና የኬሚካል ድጋፍ እንዳደረገ ተናግረዋል።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የማህበረስብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፋሪስ ኃይሉ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ባደረገው ድጋፍና ክትትል የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ በማየቴ በጣም ደስ ብሎኛል ብለው ለዚህ ውጤት መብቃት ክትትልና እገዛ ላደረጉ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ መምህራንና ባለሙያዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ዶ/ር ፋሪስ አክለውም ጠንክረን ከሰራን ውጤታማ መሆናችንን ይህ የበጋ መስኖ ስንዴ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በመስክ ጉብኝቱ ላይ ያነጋገርናቸው የወሎ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ጉግሳ ዩኒቨርሲቲው በደላንታ ወረዳ የማህበረሰቡን የበጋ መስኖ ስንዴ ውጤታማነት ለማረጋገጥ የተለያዩ እገዛዎችን እያደረገ መሆኑን ተናግረው አሁን የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ የዩኒቨርሲቲው አመራር፣ መምህራና ባለሙያዎች፣ የዞንና የወረዳ የግብርና ባለሙያዎች ክትትል ከፍተኛ እንደነበር ጠቁመዋል።
ዶ/ር ጌታቸው አያይዘውም በሰብሉ የሚስተዋለውን የስንዴ ዋግ በሽታ ለመከላከል የኬሚካል ግዥ በመፈጸም ርጭት ቢካሄድም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በመከሰቱ ውጤታማነቱ አመርቂ እንዳይሆን አድርጎታል ብለዋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ የበጋ መስኖ ስንዴ እንዲያለሙ ያደረጋቸው የደላንታ ወረዳ 01 ቀበሌ አርሶ አደሮች እንደተናገሩት እስካሁን ከነበረው የተሻለ የበጋ የመስኖ ስንዴ ማልማት እንደቻሉ በመግለጽ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ላደረገላቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው የስንዴ ዋግ በሽታ ግን እንቅፋት እንደሆነባቸው ጠቁመዋል።