Wollo University holds a graduation ceremony for veterinary medicine students who have spent the past seven years of study
Wollo University’s School of Veterinary Medicine holds a graduation ceremony for a total of 21 veterinary medicine doctors, including 13 male and 8 female students, who have completed their studies over the past seven years.
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ሰባት አመታት ያሰለጠናቸውን የእንሰሳት ህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ።
=======================================================
የካቲት 21/2016 ዓ ም (ወሎ ዩኒቨርሲቲ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጽ/ቤት)
የወሎ ዩኒቨርሲቲ የእንሰሳት ህክምና ት/ቤት ባለፉት ሰባት አመታት ያሰለጠናቸውን 13 ወንድና 8 ሴት በድምሩ 21 የእንሰሳት ህክምና ዶክተሮችን አስመርቋል። በተጨማሪም አንድ የእንሰሳት ህክምና ዶክተር በስፔሻሊቲ ፕሮግራም ተመርቋል።
በምርቃቱ ላይ የተገኙት የወሎ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታረቀኝ ትንታጉ ተመራቂዎች የኮሮና ወረርሽኝንና የሰሜኑን የርስ በርስ ጦርነት ተቋቁመው ለምርቃት መብቃታቸው የጽናት ተምሳሌቶች ናቸው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አያይዘውም ም/ፕሬዚዳንቱ እነዚህ ምሩቃን የወሎ ዩኒቨርሲቲ አምባሳደሮች በመሆናቸው ዩኒቨርሲቲውን በማስተዋወቅ በኩል የራሳቸውን ሚና እንደሚወጡ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
በዚህ የምረቃ ፕሮግራም ላይ ለተመራቂዎች የስራ መመሪያ ያስተላለፉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አወል ሰይድ የዛሬ ምርቃታቸው መነሻቸው እንጂ መጨረሻቸው እንዳልሆነ አውቀው ለቀጣይ መሻሻል እንዲተጉ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ዶ/ር አወል ተመራቂዎች ወደ ስራ አለም ሲገቡ ከዩኒቨርሲቲያቸው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር አምባሳደር እንዲሆኑ ተናግረዋል።







