ዓለም አቀፍ የደን ቀን በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተከበረ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ13ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ10ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የደን ቀን በወሎ ዩኒቨርስቲ ዋናው ግቢ “ደን እና ምግብ” በሚል መሪ ቃል ተከበረ።

ቀኑ የተከበረው በግብርና ኮሌጅ አዘጋጅነት ሲሆን የዩኒቨርሲቲው የማኔጅመንት አባላት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና ተማሪዎች ተሳትፈውበታል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንት ዶ/ር አወል ሰይድ እንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በማድረግ ፕሮግራሙን አስጀምረዋል። ደን የሰው ልጅ እስትንፋስ ከመሆኑም በላይ ለአፈር፣ ለውሃማ አካላት እና ለአጠቃላይ ብዝሃህይወት ጥበቃ አይነተኛ ሚና አለው ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል። የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ በኩልም የደን ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በጥናትና ምርምር የደንን አስፈላጊነት ማስተማርና ትውልድ ላይ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

የግብርና ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ፀጋዬ ጎበዜ ስለ ኮሌጁ ገለፃ አድርገዋል። የግብርና ኮሌጅ አራት ዲፓርትመንቶችን ይዞ የተከፈተ ሲሆን የደን ሳይንስ ትምህርት ክፍል በ2004 ዓ.ም መከፈቱን ተናግረዋል። በየጊዜው ጥናትና ምርምር በማካሄድ የአየር ንብረትን ለውጥን ተከትሎ የሚመጣን ችግር ለመቋቋምና የደን ሽፋን መጨመርን በተመለከተ ማህበረሰቡ የኔነት ስሜት እንዲኖረው መስራት ይገባል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባከበረው አለም አቀፍ የደን ቀን ቁልፍ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ደን ልማት የሰው ሰራሽ ደን ምርምር ዳይሬክተር ዶ/ር አባይነህ ደረሮ በኢትዮጵያ የደን ሽፋንን ለማሳደግ በቴክኖሎጅ የታገዘ ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡ ይህንንም ለማሳደግ በየደረጃው ግንዛቤ በመፍጠር ደኖች እንዲጠበቁ እና እንዲለሙ እየተደረገ መሆኑን ከባለፉት ዓመታት የደን ሽፋኑ እድገት ማየት ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በእለቱም በዶ/ር አመለወርቅ ቢረሳው እና ዶ/ር ሰለሞን ሙሉ የደን ቀንን የሚመለከት ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎበታል። ዶ/ር ሀዋ ወሌ የወሎ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ደን ከሰው ልጆች ጋር ያለውን ቁርኝት በመግለጽ ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ላይ ምርምር እየሰራ እንደሆነ እና ችግኞችን በመትከል ማህበረሰቡ ደንን እንዲጠብቅ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል ።

Scroll to Top