ወሎ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 1320 የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል።

በዚህ የምርቃ ፕሮግራም ላይ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች፣ የዩኒቨርሲቲው የቦርድና ማናጅመንት አባላት፣ የሚመለከታቸው የስራና የትምህርት ክፍል አመራሮች፣ አስመራቂ መምህራን እና የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አወል ሰይድ በመክፈቻ ንግግራቸው ተመራቂዎች በረጅም የትምህርት ቆይታቸው ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተቋቁመው ለዚህ መብቃታቸው የተቋሙ፣ የተማሪዎችና የወላጆች ድምር ውጤት ነው ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው በ2017 ዓ.ም የመውጫ ፈተና እንዲወስዱ ካደረጋቸው ተማሪዎች መካከልከም ከ80% በላይ ማሳለፉን ጠቅሰዋል።

በዩኒቨርሲቲው የመውጫ ፈተና ከወሰዱ የትምህርት ክፍሎች መካከል አስራ አንድ የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ ተማሪዎቻቸውን ማሳለፍ መቻላቸው ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራት ላይ እየሰራ ያለው ስራ ተጨባጭ ውጤት እያሳየ እንደሆነ ተገልጿል። በ2017 ዓ.ም 21 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው፣ ከ24 በላይ ፕሮጀክቶች ወደ ተቋሙ እንዲመጡ ተደርጎ፣ ከ20ዎቹ ጋር መፈራረም የተቻለበት የፕሮጀክት ዘመን መሆኑም በፕሬዚዳንቱ ንግግር ተጠቅሷል።

በምረቃ ፕሮግራሙ የተገኙት የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ም/ከንቲባ፣ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ አባል እና የቦርዱ ተወካይ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ የዩኒቨርሲቲውን ስራ አመራር ቦርድ ወክለው ለተመራቂዎችና ለፕሮግራሙ ታዳሚዎች መልዕክት አስተላልፈዋል። በዚህ የምረቃ መርኃ-ግብር ላይ የክብር እንግዳ በመሆን የተገኙት የአለም አቀፍ የውሃ አስተዳደር ተቋም የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር እና የእለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር አብዱልከሪም ሰይድ የራሳቸውን የ40 ዓመት የህይወት ተሞክሮ ለተመራቂዎች አጋርተዋል፤ የስራ መመሪያም ሰጥተዋል።

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ በ2017 ዓ ም ሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተና እና የመመረቂያ ነጥብ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የሰርቲፌኬት፣ የመዳሊያ እና የዋንጫ ሽልማት ተሰጥቷል። በዩኒቨርሲቲው ከሴቶች እና ከአጠቃላይ ተመራቂዎች አብላጫ ውጤት በማምጣት የሁለት ዋንጫ ተሸላሚ የሳይኮሎጅ ትምህርት ክፍል ተመራቂ ተማሪ ዚክራ ሰይድ ሆናለች።

Scroll to Top