ወሎ ዩኒቨርሲቲ 129ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በአልን የዩኒቨርሲቲው የማኔጅመንት አካላትን፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ አባት አርበኞች፣ የግቢው መምህራንና ሰራተኞች እንዲሁም ተማሪዎች በተገኙበት እለቱን በሚዘክሩ የተለያዩ ሁነቶች አክብሯል።
የክብረ በአሉን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አወል ሰይድ አድዋ በጊዜው የነበረውን ጥቁሮች አይችሉም አመለካከት የሰበረ፣ የቅኝ ግዛትን ሰንሰልለት የበጣጠሰ፣ በነጻነታችን የማንደራደርና የአልሸነፍ ባይነት ወኔን የታጠቅን ህዝቦች እንደሆንን ያሳየን የድል በአል ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር አወል አክለውም ኢትዮጵያ የነጻነት ተምሳሌት እንድትሆን ያደረገ የአለም የጥቁር ህዝቦች ድል እንደሆነም ጭምር ገልጸዋል። ይህ ድል እንዲመጣ ያደረገው የኢትዮጵያውያን የአንድነት፣ የመደማመጥና በጋራ የመቆም እሴታችን በመሆኑ ይህን እሴታችንን ጠብቀን ልናቆየው ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
በእለቱ ጥሪ ከተደረገላቸው አባት አርበኞች መካከል የደቡብ ወሎ ዞን የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ዋና ጸሃፊ አርበኛ አየለ ወ/ጊወርጊስ ወጣቱ የሃገሩን ታሪክ እንዲያውቅ፣ ለሃገሩ ፍቅር እንዲኖረውና የአባቶቹን ፈለግ ተከትሎ ሃገሩን እንዲጠብቅ መልእክት አስተላልፈዋል።
በበአሉ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ በሆኑ ምሁራን ቁልፍ ንግግሮች ቀርበዋል፡፡ ቁልፍ ንግግሮቹም “የአድዋ ድልና የኢትዮጵያውያን ስልጡንነት” በዶ/ር አሰፋ ባልቻ እንድሁም “የአድዋ ድልና የአጼ ሚኒሊክ የአመራር ሚና” በዶ/ር አለማየሁ እርቅይሁን የቀረቡ ነበሩ።
በዚህም በአጼ ምኒሊክ እና በእቴጌ ጣይቱ የበላይ አመራር ሰጭነት ከጣሊያን ከተቃጣብን አረመኔያዊ ተግባር አንጻር ኢትዮጵያ ምላሽ የሰጠችው በጭካኔ ሳይሆን በስልጡንነት፣ በመልካም አቀራረብ፣ በሰብአዊ ክብር አያያዝ እና በፍትህ እንደነበር የስንቅና የትጥቅ አቅርቦቱ እንዲሁም የምርኮኛ አያያዙ ለአብነት ተጠቅሰዋል። በሌላ በኩል የንጉሠ ነገሥቱ የዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ የአመራር ሚና፣ በጦርነቱ ጊዜ የነበረውን የሃገር ፍቅር ስሜት፣ የጦር ስልት፣ የአባቶችና የእናቶች ተጋድሎ ምን እንደሚመስል ተዳሷል።
አድዋ ጊዜ የማይሽረው ታሪካዊ ክንውን እንደሆነና ኢትዮጵያዊነት የትውልድ ቅብብሎሽ ውጤት በመሆኑ የአሁኑ ትውልድ ከአድዋ አንድነትንና መተባበርን መማር እንዳለበት ተጠቁሟል።
የመርሃ ግብሩን የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ጌትነት መልአክ አድዋ ጥቁሮችን አንድ ያደረገ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ከአድዋ የሃገር ፍቅርን፣ አንድነት፣ መቻቻልን፣ የሰው ልጆችን እኩልነት ተምረን አባቶቻችን በሄዱበት መንገድ ልንሄድ ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል
በመርሃግብሩ አድዋን የሚዘክሩና የጀግንነትን ብሎም የአልሸነፍ ባይነትን ወኔ የሚቀሰቅሱ የተለያዩ የኪነጥበብ ስራዎች በወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድን የቀረበ ሲሆን በመጨረሻም የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ተዘምሮ መርሃግብሩ ተጠናቋል።












