ወሎ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ መካከል የተሻለ የሰላም እሴት ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችል ፕሮጀክት መጀመሩን ገለጸ

መጋቢት 2/2016 ዓ ም (ወዩ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጽ/ቤት)

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከሀገር ውጭ የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ፣ ከሀገር ውስጥ ደግሞ ከመቀሌና ሰመራ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በማህበረሰብ መካከል የሰላም እሴት ለመገንባት የሚያስችል የወጣቶች ካርታ አዘጋጅ (youth mapper) ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።

ይህን ፕሮጀክት ወደ ስራ ለማስገባት ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ፣ ሰመራና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ ወጣቶች ስልጠና እንዲያገኙ አድርጓል። ስልጠናውን የወሰዱ ወጣቶችም በአማራ፣ ትግራይና አፋር ማህበረሰብ መካከል የሰላም እሴት ለመገንባት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በስልጠናው ላይ የተገኙት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ በሰሜኑ የተነሳው የርስ በርስ ጦርነት በሴቶችና በወጣቶች ላይ የጣለው ጠባሳ ዳግም እንዳይከሰት ሰልጣኝ ወጣቶች ከስልጠናው ያገኛችሁትን መነሻ በመጠቀም በማህበረሰብ መካከል ጠንካራ የርስ በርስ ግንኙነት እንዲፈጠር መስራት ይጠበቅባችኋል ብለዋል።

አያይዘውም ፕሬዚዳንቱ ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዲሆን የወሎ፣ መቀሌና ሰመራ ዩኒቨርሲቲዎች ማንኛውንም ሀላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ እንደሆኑ ጠቁመዋል።

ከአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ጋር ከምንሰራቸው ስምንት ትልልቅ ፕሮጀክት መካከል የወጣቶች ካርታ አዘጋጅ (youth mapper) ፕሮጀክት አንዱ ነው ያሉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አወል ሰይድ ፕሮጀክቱ የወጣቶች በመሆኑ በነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ላይ ለመስራት መደላድል ሰለሚፈጥር በጥንቃቄ እና በጥልቀት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።

ስልጠናው ነገሮችን እንደት ማየት፣ ማዘጋጀትና መምራት እንዳለብን መነሻ እውቀት ያገኘንበት ነው ያሉት ከመቀሌ ወሎና ሰመራ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ሰልጣኞች ፕሮጀክቱ ማህበረሰብ ከማህበረሰብ በማገናኘት የሰላም እሴት ለመገንባት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

Scroll to Top