ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ከ 8 መቶ በላይ ተማሪዎችን ለ16ኛ ጊዜ በዛሬው ዕለት በአዲሱ የልዕለ ህክምና ካምፓስ አስመርቋል።
በዚህ የምረቃ ፕሮግራም ላይ ለተመራቂዎች የስራ መመሪያ ያስተላለፉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ፕሬዚዳንትና የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አወል ሰይድ ዩኒቨርሲቲው ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት በማስተዋወቅ የዛሬ ተመራቂዎች ምርቃታቸው መነሻቸው እንጂ መጨረሻቸው እንዳልሆነ አሳውቀው በዚህ ተለዋዋጭ አለም ውስጥ አሸናፊ ሆኖ ለመዝለቅ ከተቀጣሪነት ይልቅ ስራ ፈጠራ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ምክር ለግሰዋል፡፡ በተጨማሪም ዶ/ር አወል ተመራቂዎች ወደ ስራ አለም ሲገቡ ከዩኒቨርሲቲያቸው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር አምባሳደር እንዲሆኑ ገልጸው በመጨረሻም የምረቃ ስነስርአቱ የተሳካ እንዲሆን የሰሩ የኮሚቴ አባላት፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና የጸጥታ አካላትን አመስግነዋል።
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤናው ዘርፍ የሰው ሃብት ልማት ማሻሻያ መሪ ስራ አስፈጻሚና የእለቱ የክብር እንግዳ አቶ አሰግድ ሳሙኤል ለተመራቂዎች የስራ መመሪያ ያስተላለፉ ሲሆን ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በቀሰሙት እውቀትና ክህሎት በፍጹም ቅንነት አገራቸውን እንዲያገለግሉ አሳስበዋል::
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሬጅስትራርና አልሙናይ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ገዛኸኝ አሰፋ በአደረጉት ገለጻ በመጀመሪያ ዲግሪ 255 ወንድ 116 ሴት በድምሩ 371፤ በሁለተኛ ዲግሪ 270 ወንድና 90 ሴት በድምሩ 360 ተማሪዎችን እንዲሁም በመምህራንና ስነባህሪ ተቋም የከፍተና ዲፕሎማ/HDP/ ተመራቂዎች ወንድ 62 ሴት 49 ድምር 82 በተጨማሪም አንድ በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ኮሌጅ የሂሳብ ትምህርት ክፍል በአናሊስት ትምህርት መስክ በ3ኛ ዲግሪ ተመርቋል በአጠቃላይ ወንድ 589 ሴት 225 ድምር 814 ተማሪዎች መመረቃቸውን ተናግረዋል።