128ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል “የአድዋ ድል፣ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት አርማ!” በሚል መሪ ቃል በወሎ ዩኒቨርሲቲ በድምቀት ተከበረ

የካቲት 21 ቀን 2016 ዓ.ም (ወሎ ዩኒቨርሲቲ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጽ/ቤት)

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ቢሮ ጋር በመተባበር የአድዋን 128ኛ ዓመት መታሰቢያ ድል በዓል በወሎ ዩኒቨርሲት ዋናው ግቢ አክብሯል።

ዶ/ር መንገሻ አየነ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት እለቱን በማስመልከት የመክፈቻና የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባን፣ ጀኔራል ዘውዱ ሰጣርጌ የ801ኛ ኮር ዋና አዛዥና የደሴ ከተማና አካባቢው ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢን መልዕክት እንዲያስተላልፉ ጋብዘዋል።

ተጋባዦቹ በየተራ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በተለይ ጀኔራል ዘውዱ ሰጣርጌ በንግግራቸው እለቱ የመላው ጥቁር ህዝብ የነጻነት ተምሳሌት መሆኑን፣ የተቆጣን ህዝብ በመሳሪያ ብዛት እና በቴክኖሎጅ የበላይነት ማሸነፍ እንደማይቻል ትምህርት የተወሰደበት መሆኑን፣ ጀግንነት የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ እሴት የተደረገበት፣ እጅግ ከፍተኛ የውጊያ ጥበብ የታየበት፣ በተቃራኒውም በነጮች በክፉ ዓይን እንድንታይና ጠላቶቻችን እንዲበዙ ያደረገ ክስተት መሆኑን ገልፀዋል። አያይዘውም ድሉ ልንማርበት የሚገባ ከመሆኑም በላይ የጠላቶቻችንን ክንድ ለመቋቋም በአንድነት ልንዘጋጅበት የሚገባ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።

እለቱ ድሉ በሚዘክሩ በደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ በተዘጋጀ የፎቶግራፍ አውደርዕይ፣ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የባህል ቡድን፣ በሙዚቃና ትያትር ትምህርት ክፍሎች መምህራንና ትያትር ተማሪዎች በቀረቡ ልዩልዩ ጣዕመዜማዎች፣ ትያትርና በጥናታዊ ጽሑፍ አቅትቦቶች ታስቦ ውላሏል።

ጥናታዊ ጽሑፎች በወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የቀረቡ ሲሆኑ ርዕሶቻቸው “የአድዋ ድልና የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ የሃሳብ ልዕልና” (ዶ/ር አለማየሁ እርቅይሁን)፣ “የአድዋ ድልና የጣሊያን ምርኮኞች አያያዝ” (ዶ/ር አሰፋ ባልቻ) እና “አድዋ ለሃገር ግንባታ:- ሃገራዊ ማንነት፣ እሴቶችና ጥቅሞች” (አቶ ይመር ዓሊ) የሚሉ ነበሩ።

በመጨረሻም የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ሃዋ ወሌ የመዝጊያ ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም በሚቀጥለው ዓመት ከዚህ በተሻለ እንደሚከበር ጠቁመዋል።

በድል በዓሉ ላይ ዶ/ር ካሳ ሻውል የመቅደላ አምባ የኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፣ አርበኞች፣ የወሎ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ኃላፊዎች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና ተማሪዎች እንዲሁም የሐይማኖት አባቶች እና የሃገር ሽማግሌዎች ታድመዋል።

Scroll to Top