ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተከበረ


በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ114ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ የተከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 😎 በወሎ ዩኒቨርሲቲ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

ሴቶች የሚደርስባቸውን ከፍተኛ የስራ ጫና፣ ጾታዊ ጥቃት እና የመብት ጥሰት በማስቀረት እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ይከበራል። የዘንድሮው መሪ ቃልም “ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል!” የሚል ነው።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሴቶች ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መነሻ የተጣለበት እለት መሆኑን የወሎ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺወርቅ አሰፋ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ገልፀዋል። ዩኒቨርሲቲው የሴቶችን አቅም ለማሳደግ የሴቶችን የአቻ ላቻ ስልጠና፣ ፎረም እና የክለብ አደረጃጀቶችን በማቋቋም አጠናክሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባካሄደው በዚህ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የሴቶችን ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በዩኒቨርሲቲው የተቋቋሙት የሴት መምህራን ፎረም እና የኔድርሻ የሴት መምህራን በጎ አድራጎት ማህበር ስለ አጠቃላይ ዓላማቸው ገለጻ አድርገዋል።

በእለቱ ከአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ለትምህርታዊ ስልጠና የመጡት መምህርትና ተመራማሪ ዶ/ር ሞሊ ኦት ለተሳታፊ ሴቶች ያላቸውን ልምድ አጋርተዋል። በተጨማሪም ቀኑን የተመለከቱ አነቃቂ መልዕክቶች፣ ግጥሞች እና ሙዚቃዎች ቀርበው ፕሮግራሙ ተጠናቋል።

Scroll to Top