ጥር 8/2016 (ወሎ ዩኒቨርሲቲ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጽ/ቤት
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስተር ጋር በመተባበር የሎጎ ሀይቅን መልሶ በዘላቂነት ለማልማት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል።
በውይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶ/ር ሰይድ ሁሴን የሎጎ ሀይቅን መልሶ ለማልማት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሎጎ ሀይቅ መልሶ የማልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር አሰፋ ተሰማ የሎጎ ሀይቅን መልሶ ለማልማት ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስተር ጋር በቅንጂት ከ2012 ዓ ም ጀምሮ በሁለት ምዕራፍ የሰሯቸውን ስራዎች በዝርዝር አቅርበዋል።
በመወያያ ሰነዱ የሎጎ ሀይቅን በዘላቂነት ለማልማት በፕሮጀክቱ አፈጻጸም ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፣ የተወሰዱ መፍትሄዎችና በሀይቁ ላይ የታዩ ለውጦች በማስረጃ ቀርበዋል።
የፕሮጀክቱን የሪፖርት ሰነድ መነሻ በማድረግ ሰፊ ውይይት ያደረጉት ባለድርሻ አካላት የሎጎ ሀይቅን መልሶ ለማልማት ከፍተኛ ርብርብ እንድሚያስፈልግ በመግልጽ ፕሮጀክቱን ከሀገር ውስጥና አለም አቀፍ ፕሮጀክቶች ጋር የማስተሳሰር ስራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
አያይዘውም የውይይቱ ተሳታፊዎች የሎጎ ሀይቅን በዘላቂነት ለማልማት የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በመጨመር ሀብት የማሰባሰብ ተግባር ጭምር ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ ውሃና ኢነርጅ ሚኒስተር፣የሚመለከታቸው ከደቡብ ወሎ ዞን፣ ከሀይቅ ከተማ፣ ከተሁለደሬና ወረባቦ ወረዳዎች የመጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።