በዩኒቨርሲቲዎች እና በኢንዱስትሪዎች መካከል ትስስር መፍጠርን በተመለከተ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደረገ

የትምህርት ጥራት፣ ሃብት መጋራት፣ ፈጠራን እና ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማሳደግ በኩል በዩኒቨርሲቲዎች እና በኢንዱስትሪዎች መካከል ትስስር መፍጠርን በተመለከተ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በወሎ ዩኒቨርሲቲ ደሴ ግቢ ውይይት ተካሄደ።

በምክክር መድረኩ ላይ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ልዩልዩ የስራና ትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ የኢንደስትሪዎች፣ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና እንዲሁም የምርምር ተቋማት ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። ውይይቱ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ተግባር ዩኒቨርሲቲ እያደረገ ያለውን የሽግግር ሂደት ለማሳለጥ የአጋር አካላት ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ከአጋር አካላት ጋር ስለሚኖረው ትስስር መምከርን አላማ ያደረገ ነው።

ከዚህ በመነሳትም በዋናነት አራት ተቋማትን ማለትም በአካባቢው ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትን፣ የፌደራል እና የአማራ ክልል የምርምር ተቋማትንና የአምራች ዘርፉ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ነው። በተጨማሪም ከደሴ ከተማ፣ ከኮምቦልቻ ከተማ፣ ከደቡብ ወሎና ከኦሮሚያ ልዩ ዞን የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤት ኃላፊዎች ተሳትፈውበታል።

በውይይቱ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሃዋ ወሌ ሲሆኑ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ብርሃን አስማሜ የመክፈቻ ንግግር አድርገው ውይይቱን በይፋ አስጀምረዋል።

በሃገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ተቋማትንና የኢንዱስትሪዎችን ትስስር በተመለከተ በአጀንዳነት ስለተያዘው ሪፎርም፣ የትስስሩን አላማ፣ የትኩረት አቅጣጫዎችንና ሊኖሩ የሚችሉ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ውይይት የተደረገባቸው ጉዳዮች ናቸው። በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ተጠባባቂ መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሰራዊት ሀንዲሶ፣ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር አሳምን አያሌው፣የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዓለም አቀፍ ግንኙነትና አጋርነት ዳይሬክተር ዶ/ር አስረሴ ሞላ እና በኢትዩጵያ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ተወካይ አቶ አዳነ ቸሩ የመወያያ ጽሁፍ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

በመጨረሻም ከባለድርሻ አካላቱ ጋር ወደፊት በትብብር ለመስራት የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል። የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ጀኔራል ዶ/ር አስማረ ደጀን የተነሱ ሃሳቦች ወደተግባር ተለውጠው ፍሬ ማፍራት እንዲችሉና ዘላቂነት ያለው ልማትን ማምጣት እንዲቻል የሁላችንም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ነው ብለዋል።

Scroll to Top