በወሎ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ጥበባት ት/ቤት የቴአትር ጥበባት ት/ክፍል የቀድሞ ተመራቂዎች ጋር በዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ የአልሙናይ መድረክ ተዘጋጀ
በቀድሞ የወሎ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ት/ክፍል ተመራቂዎች (አልሙናይ) እና አሁን በትምህርት ላይ ባሉ የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች መካከል የልምድ ልውውጥና የውይይት መድረክ በዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው ደሴ ግቢ ተዘጋጅቷል።
የትምህርት ክፍሉ አልሙኒ በ2016 ዓ.ም ሲመሰረት በትምህርት ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች የልምድ ልውውጥ፣ የክህሎት ስልጠናና የገበያ ትስስር የሚፈጥሩባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት ዋና አላማው ያደረገ ነው። ይህንን አላማ መሰረት በሚድረግ የ2008 ዓ.ም የወሎ ዩኒቨርሲቲ የቴያትር ጥበባት ት/ክፍል ተመራቂ የነበረችው አርቲስት ፀዳለ ጥበቡ የእለቱ እንግዳ ሆናለች፡፡
ደሴ ከተማ ተወልዳ ያደገችውና ወሎ ዩኒቨርሲቲ ያፈራት አርቲስት ፀዳለ ጥበቡ ከወሎ ዩኒቨርስቲ ከተመረቀች በኋላ ደረጃቸው ከፍ ያሉ በርካታ የፊልምና የሚዲያ ስራዎች ላይ በዋና አዘጋጅነት ሰርታለች። አርቲስቷ በመድረኩ ላይ ተማሪዎች ከትምህርት ተቋም ሲወጡ ስለሚጠብቃቸው አለም ሰፊ የስራ ልምዷን ለተማሪዎች አጋርታለች።
አርቲስቷ ተማሪዎች ትምህርት ከጨረሱ በኋላ በስነ-ጥበብ እና ሚዲያ ኢንዱስትሪው ውስጥ አሸንፎ ለመውጣት ማድረግ ስለሚገባቸው ዝግጅቶች አብራርታለች። በተለይም ሴቶች በኢንዱስትሪው ውስጥ ብርቱ ተሳታፊ የሚያደርጋቸውን ግንዛቤ አስጨብጣለች። ከትወናና ፕሮግራሞችን ከማቅረብ ባለፈ በጥበብ አለም ውስጥ ተማሪዎች ለሚኖራቸው ሚና፣ የሞያ ብቃትና ስነ-ምግባር በጥያቄና መልስ ሰፊ ማብራሪያ ከስራ ገጠመኞቿ ጋር በማጣቀስ አቅርባለች፡፡



