ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከኢንዱስትሪዎችና ሌሎቸ መሰል ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ጉባኤ አካሄደ።

የተግባር ሳይንስ (Applied University) ተብለው ከተለዩ 15 ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ የሆነው ወሎ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ትምህርቶችን ከኢንዱስትሪው ጋር ለማስተሳሰር የሒሳብ – ኢንዲስትሪ ትስስር ጉባኤ አካሄዷል።

የጉባኤው ተሳታፊዎችን እንኳን ወደ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና ሀይማኖታዊ መናገሻ ወሎ በሰላም መጣችሁ ያሉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርን ማጠናከር በሒሳብ፣ በፊዚክስና ሌሎች ጠንካራ የሳይንስ ትምህርቶች በኢንዱስትሪው ውስጥ ያላቸውን ሚና አጉልቶ ለማሳየት በር ይከፍታል ብለዋል።

የሒሳብ ኢንዱስትሪ ትስስር ጉባኤ መካሄዱ ወቅቱ ከሚፈልገው ገበያ ጋር የተናበበ ምሩቃንን ለማፍራት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ያሉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አወል ሰይድ ዩኒቨርሲቲው ተልዕኮውን ለመወጣት ከኢንዱስትሪዎች ጋር የስርዓተ ትምህርት ቀረጻ ጭምር እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የተግባር ሳይንስ ትምህርቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ከተግባር ተኮር ተቋማት ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር ይገባናል ያሉት የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሳ አዳል በኮሌጁ ያሉ ስምንት ትምህርት ክፍሎች ከኢንዱስትሪዎችና መሰል ተቋማት የዳሰሷቸውን ጥናቶች የሚያሳይ አውደ ርዕይ ከማሳየት ጀምረን ትምህርት ክፍሎችን ከተቋማት ጋር የማገናኘት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

አያይዘውም የኮሌጅ ዲኑ በኮሌጁ ያሉ ትምህርት ክፍሎች ከኢንዱስትሪዎችና መሰል ተቋማት ጋር በመቀናጀት የስርዓተ ትምህርት ቀረጻ በማካሄድ ገበያው የሚፈልገውን የሰው ሀይል ለማፍራት ጉባኤው በር ይከፍታል ብለዋል።

በጉባኤው የተሳተፉት የኢንዱስትሪ ተወካዮች የሒሳብ ኢንዱስትሪ የትስስር ጉባኤ መካሄዱ ዩኒቨርሲቲዎች በኢንዱስትሪዎች ያሉትን ክፍተቶች በጥናት በመለየት የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሳደግ ይረዳል ሲሉ ገልጸዋል።

የሒሳብ- ኢንዱስትሪ ትስስር መፈጠሩ ኢንዱስትሪው በተግባር የሰለጠና የሰው ሀይል ከዩኒቨርሲቲዎች ለማግኙት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ሲሉ ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በጉባኤውም ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት በማካሄድ ጉባኤው ተጠናቋል።

Scroll to Top