ወሎ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት “የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ፖሊሲ እና አተገባበር ጥናት” ለማካሄድ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ወሎ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት በ13/03/2016 ዓ/ም “የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ፖሊሲ እና አተገባበር ጥናት” ለማካሄድ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡፡

በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የወሎ፣ የጅማ፣ የሀዋሳና ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች የጥናትና ምርምር ም/ፕሬዚዳንቶች፣ ተመራማሪዎች፣ የጥናቱ አስተባባሪዎች እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። በወሎ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት የሚከናወነው ይህ ጥናት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ፖሊሲና አተገባበር ጥናትም ዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን፣ ሃገራዊ ፍላጎቶችን እንዲሁም ሁሉንም የዳያስፖራ አቅሞች ከሁሉም የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት መጠቀምን ታሳቢ አድርጎ እንደሚከናወን አቅጣጫ ተቀምጧል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተወካይና የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር አወል ሰይድ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባባር በዕውቀት ላይ በመመስረት የዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማትና ተሳትፎ ስራዎችን ለማከናወን እያደረገ ስላለው ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸው፣ ዩኒቨርሲቲያቸው ከሶስቱ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባባር ጥናቱን ያከናውናል ብለዋል።

ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ ባስተላለፉት መልዕክት ደግሞ አገልግሎቱ በዘርፉ የሚያከናውናቸው ስራዎች በዕውቀት የሚመሩ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽና ዕውቅና ያላቸው እንዲሆኑ ለማድረግ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ከከፍተኛ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ጋር በትብብር በመሰራት ላይ ያሉ ጥናቶች ዋነኛ ዓላማም እነዚህኑ ግቦች ማሳካት ነው ብለዋል። አገልግሎቱ ከጅማ፣ ከወሎ፣ ከሀዋሳና ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እያከናወናቸው ያሉ ተከታታይ የጥናት ስራዎችም በዚሁ ዕይታ ውስጥ የተቃኙ መሆናቸውን አስታውሰው፣ የጥናት ውጤቶችን በፍጥነት በመተግበር ለውጤታማነት መስራትም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

የዚሁ ጥናት አካል የሆነውና በጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት እንዲሁም በቀሪዎቹ ሶስት ዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፎ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በዳያስፖራ ዕውቅት፣ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትኩረት አድርጎ የተደረገው ጥናት በዕለቱ ርክክብ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ‘የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ፖሊሲ እና አተገባበር ጥናት’ን ለማከናወን የተዘጋጀው የስራ እቅድ ቀርቦ በተሳታፊዎች ሃሳብና አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡

Scroll to Top