ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ወሎ ልዕለ ሕክምና እና ማስተማሪያ ሆስፒታል ልዕለ ሕክምና ካምፖስ የመማር ማስተማር ስራውን በይፋ መጀመሩን አስታወቀ።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በደሴና ኮምቦልቻ ግቢዎች ስልጠናዎችን ከመስጠት ባሻገር ሶስተኛውን የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ወሎ ልዕለ ሕክምና እና ማስተማሪያ ሆስፒታል ልዕለ ሕክምና ካምፖስ በመክፈት ማሰልጠን ጀምሯል። ካምፓሱም ዩኒቨርሲቲው በጤናው ዘርፍ ለሚሰለጥነው የሰው ኃይል ጥራት የራሱን ድርሻ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ከብዙ ድካም በኋላ ሶስተኛውን ልእለ ህክምና ካምፖስ ለመክፈት በቅተናል ያሉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ ካምፖሱ ወደ ስራ እንዲገባ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት፣ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮችና መላው የተቋሙ ማህበረሰብ ላደረጉት የላቀ አስተዋጽኦና ጥረት እውቅና ሰጥተዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው በተግባር በተደገፈ ስልጠና ምሩቃንን ከማፍራት ባሻገር ራሳቸውን ካልተገባ ተግባር ያራቁ፣ በስነ ምግባር የታነጹና ህዝባቸውን በቅንነት የሚያገለግሉ ሙያተኞችን ለማፍራት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

አያይዘውም ፕሬዚዳንቱ በሕክምና ሳይንስ ዘርፍ ጥራት ያላቸውን ተማሪዎች ለማውጣት ማስተማሪያውን አሁን ካሉት የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች በተጨማሪ ግብአቶችን የማሟላት ስራ ይሰራል ሲሉ ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ አጭር ገለጻ ያደረጉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አወል ሰይድ ካምፓሱን ስራ ለማስጀመር የተማሪ መኝታ ክፍል፣ የመማሪያ ክፍል፣ ክሊኒክ፣ ቤተ መጽሀፍት፣ ቤተ ሙከራ፣ የአስተዳደር ቢሮ ወዘተ. መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት የተጓዙበትን ርቀት አሳይተዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ወሎ ልዕለ ህክምና እና ማስተማሪያ ሆስፒታል የልዕለ ሕክምና ካምፖስ ዲን ዶ/ር መታደል አዳነ በካምፖሱ ስራ መጀመር የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፣

እንደ ዶ/ር መታደል ገለጻ ልዕለ ሕክምና ካምፓሱ አሁን ባለበት ደረጃ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት በመሆኑ ጥራት ላለው የተግባር ተኮር ትምህርት ውጤታማነት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ገልፀዋል።

አያይዘውም ዲኑ ካምፓሱ በ1 ሺህ 2 መቶ 20 ተማሪዎች ስራ የጀመረ ሲሆን ወደፊት ግንባታዎች ሲጠናቀቁ የመቀበል አቅሙ ከ2 ሺህ 1 መቶ በላይ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

በመጨረሻም የፕሮግራሙ ታዳሚዎች በካምፓሱ ያሉትን የስራ እንቅስቃሴዎች ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ውይይት ተካሄዶ መርሃ ግብሩ ተጠናቋል።

Scroll to Top