የወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ከቀለም ሜዳ ቴክኖሎጂ ጋር በመተባበር ለመምህራን እና ተማሪዎች ለሶስት ተከታታይ ቀናት ስልጠና ሰጠ።
ይህ ስልጠና ሶስት የተለያዩ መርሃ ግብሮች ያካተተ ሲሆን፤ የኢንዱስትሪ ልምድ እና አመሰራረት በሚል ርዕስ የቀለም ሜዳ ቴክኖሎጂ መስራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ የድርጅታቸውን የኢንዱስትሪ ልምድ እና አመሰራረት አስመልክቶ ሰፊ ገለፃ አቅርበው፣ ውይይት ተካሂዷል ።
ሁለተኛው ርዕስ “Full-Stack Development” በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባላቸው የቀለም ሜዳ ቴክኖሎጂ የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች ስልጠናው ተሰጥቷል። ይህ ስልጠና ዩኒቨርሲቲው ተግባር ተኮር በመሆኑ፣ ተማሪዎች የኢንዱስትሪውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ትምህርት እንዲያገኙ ማስቻል ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
ሶስተኛው ርዕስ “Standardization and Program Accreditation” ስልጠና ሲሆን፤ ለትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና የስርዓተ ትምህርት ክለሳ ኮሚቴ አባላት በዘርፉ ISO Certified በሆኑ ባለሙያዎች ተሰጥቷል።
በመዝጊያው መርሃ ግብር ላይ የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር መላኩ ታመነ ተገኝተው ይህ አይነቱ ተግባር ተኮር ስልጠና ከዩኒቨርስቲው የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸው፣ ስልጠናው ቀጣይነት እንዲኖረው አሳስበዋል። በተጨማሪም መምህራንም ስልጠናውን ወደ ተግባር በመቀየር ችግር ፈቺ ሥራዎችን እንዲሰሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የቀለምሜዳ ቴክኖሎጂ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገብረመድህን መኮንን በበኩላቸው፣ የቀለም ሜዳ ቴክኖሎጂ በኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ መምህራንና ተማሪዎች በጋራ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ አይነት መድረክ ለመምህን እና ለተማሪዎች ልምድን ማካፈል ከፍተኛ ደስታ ይሰጣል ብለዋል ።
የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ዲን አቶ ጋሻው በቀለ በበኩላቸው ፤ በዩኒቨርሲቲው በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ፕሮግራሞች ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ እውቅና እንዲኖራቸው እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፣ እንደ ተግባር ተኮር ዩኒቨርሲቲ ፕሮግራሞችን ከኢንዱስትሪ ፍላጎት ጋር ለማጣጣም በጋራ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ፣ ከሌሎች መሰል ኢንዱስትሪዎች ጋር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።




