በወሎ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ፕሮጀክቶችን የመቅረጽና የማስተዳደር ሂደትን በተመለከተ የልምድ ልውውጥ ተካሄደ

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶችን የመቅረጽና ፕሮጀግቶችን የማስተዳደር ሂደትን በተመለከተ በዘርፉ ልምድ ካላቸው የሶስቱም ግቢ የኮሌጅ ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና ሰራተኞች እንዲሁም ነባር መምህራን ጋር የልምድ ልውውጥ ተካሄደ።

በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አወል ሰኢድ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት ከተለያዩ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባባር ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመዋል።

ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር አጋር አካላት ጋር በትብብር ለመስራት ምሁራን የሚያቀርቧቸው የምርምር ጽሁፎች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ ይህ የልምድ ልውውጥ መድረክ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን የፕሮጀክት ጽሁፎችን በማቅረብ ረገድ ያሉ ልምዶችን በማጠናከር እርስበርስ ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው በተሰጠን ተልእኮ ልክ በመማር ማስተማር በምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት መስራት ስንችል ነው። በመሆኑም እንደዚህ አይነት መድረኮች የእርስበርስ ግንኙነትን በማጠናከር ሃሳቦችን ወደ ስትራቴጂ ቀይሮ ለመስራት ወሳኝ ሚና ስላላቸው ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ድርጅቶች ተቀባይነት አግኝተው የተጀመሩ አምስት ፕሮጀክቶች ላይ የፕሮጀክቱን አጀማመር፣ ሂደትና አፈጻጸም፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና መልካም ተሞክሮዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ገለጻ በፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በውይይቱም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለማሸነፍ የሚያስችሉ ሂደቶችንና የዩኒቨርሲቲውን ሚና በተመለከተ ከተሳታፊዎች ሃሳብ አስተያየቶች ቀርበው ከዩኒቨርሲቲው የማኔጅመንት አባላት መልስ ተሰጥቶባቸዋል።

በመጨረሻም የምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶ/ር ሰይድ ሙሄ ባለፉት አመታት በዩኒቨርሲቲው ውጤታማ የምርምር ስራዎች እየተከናወኑ እንደነበር ገልጸው ይህ የልምድ ልውውጥ በቀጣይ የተሻለ ስራን ለመስራት የተማማርንበት ነው ብለዋል። በቀጣይም ጽ/ቤቱ የማህበረሰቡን ችግር ፈች የሆኑ የምርምር ሰራዎችን ለማከናወን በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

Scroll to Top