በወሎ ዩኒቨርሲቲ የጭብጥ ተኮር ምርምር ዲዛይንና አሰራር ስልጠና ተሰጠ

በወሎ ዩኒቨርሲቲ ከሶስቱም ግቢ ለተውጣጡ ተመራማሪወች፣ ዲኖች፣ ምክትል ዲኖች፣ አስተባባሪዎች፣ ለኮሌጅና ትምህርት ቤት አመራሮች እንዲሁም ለግዥና ፋይናንስ ኤክስኪዩቲቭ ማናጀሮች የጭብጥ ተኮር ምርምር ዲዛይንና አሰራር ላይ ያተኮረ የሶስት ቀናት ስልጠና ተሰጠ።

በስልጠናው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የወሎ ዩኒቨርስቲ አስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር ታረቀኝ ትንታጉ ዩኒቨርሲቲያችን የተግባር ሳይንስ ዩኒቨርስቲ ከመሆኑና ካሉት የልህቀት ማዕከላት (Center of Excellence) አንጻር ጭብጥ ተኮር የምርምር አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ስለሆነም ስልጠናው ጭብጥ ተኮር የጥናትና ምርምር ዘዴን ተግባራዊ ለማድረግ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

የምርምር ህትመት ስነምግባርና ስርፀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰይድ ሙሄ በበኩላቸው ጭብጥ ተኮር የምርምር ዘዴ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት ሚኒስቴር አቅጣጫ የመጣ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ከጥቅምት 2017 ዓ.ም ጀምሮ የማስተዋወቅ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

ይህ ስልጠናም በ2018 ዓ.ም ለሚሰሩ ጭብጥ ተኮር የምርምር ስራዎች በምርምር ዘዴው በጽንሰ ሃሳብና በአተገባበር ረገድ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት፣ የጭብጥ ተኮር ምርምር አሰራርና አስተዳደርን በተሳለጠ መልኩ የሚያካሂድበትን ሁኔታ ለመፍጠር፣ ጊዜን፣ ሀብትንና ጉልበትን በአግባቡ ተጠቅሞ በትብብር ለመስራት የሚያስችል ግንዛቤ እንደሚያስጨብጥ ብሎም የዪኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርን ከመፍጠር አንጻር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተገልጿል።

ስለጠናው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጡት ምሁራን ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ እና ፕሮፌሰር በላይ ተፈራ የተሰጠ ሲሆን ተሳታፊዎች የወሰዱትን ስልጠና ለሌሎች እንዲያሰርፁና ወደ ተግባር ቀይረው እንዲጠቀሙበት የወሎ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጅ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ልዮ ረዳት ዶ/ር ሰይድ ሁሴን አሳስበዋል።

Scroll to Top