በወሎ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አጠቃቀም ማሻሻያ ስልጠና ለመምህራን እየተሰጠ ነው

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አጠቃቀም ማሻሻያ ስልጠና ከሁሉም ኮሌጆችና ትምህርት ክፍሎች ለተውጣጡ ከ150 በላይ ለሆኑ መምህራን በሶስቱም ግቢ እየተሰጠ ይገኛል።

የአካዳሚክ ጉዳዮች ተወካይ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ብርሃን አስማሜ ስልጠናው እንግሊዝኛ ቋንቋ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የማስተማሪያ ቋንቋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ትምህርት ሚኒስቴር ሁሉም የዩኒቨርሲቲ መምህራን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቁ ሆነው እንዲገኙ በያዘው ሪፎርም መሰረት ለመምህራን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ስልጠና መሰጠት መጀመሩን ገልጸዋል።

ስልጠናው የመምህራንን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት በማሳደግ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያጠናክርና ከፍተኛ ተጽእኖ ሊፈጥር የሚችል መሆኑም ተናግረዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር በተደረገው ጥናት በሀገራችን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት ችግር ከሚታይባቸው ተቋማት መካከል ዩኒቨርስቲዎች ተጠቃሾች መሆናቸውን በእንግሊዝኛ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የስልጠናው አስተባባሪ ዶ/ር እንግዳሰው ንጉሴ ገልፀዋል።

ይህን ችግር ለመፍታት በትምህርት ሚኒስቴር አራት የስልጠና ሞጁሎች (ለዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ለተማሪዎች፣ ለአስተዳደር ሰራተኞችና በአካባቢው ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች መምህራን) መዘጋጀታቸውንና አሁን ላይ ለዩኒቨርሲቲው መምህራን ስልጠናው እየተሰጠ ነው።

ስልጠናው መምህራን ትክክለኛ ቋንቋን እና ቴክኖሎጅን ክፍል ውስጥ መጠቀም እንዲችሉ እንዲሁም ማሰልጠኛና ማስተማሪያ መሳሪያዎችን ማዘጋጀት እንዲችሉ አቅም የሚፈጥር በመሆኑ በተለያየ ዙር ለሁሉም መምህራን የሚሰጥ ይሆናል።

ይህ ስልጠና ለአንድ አመት የሚቆይ ነው ሲሆን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል መምህራንና በስልጠናው አስተባባሪዎች የሚሰጥ ነው።

ስልጠናው እንዳለቀ በትክክል ያጠናቀቁ ሰልጣኞች ተመዝነው የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጥና ከመምህራን የሙያ እድገት መሰላል ጋር የተገናኘ እንደሚሆንም ተገልጿል።

Scroll to Top