በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ

24ኛው በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም “ትብብር እና አጋርነት ለሁለተናዊ ማህበረሰብ ለውጥ” በሚል መሪ ቃል በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ።

በፎረሙ ላይ ከፌዴራልና ከክልሉ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች፣ በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችና ም/ፕሬዚዳንቶች፣ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንቶች፣ የደ/ወሎ ዞን እንዲሁም የደሴና ኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አወል ሰይድ የፎረሙን ተሳታፊዎች እንኳን ወደ ፍቅር እና የጥበብ መናገሻ ወደሆነችው ደሴ ከተማ በሰላም መጣችሁ በማለት የእንኳን ደህና መጣሁ ንግግር አድርገዋል።

ዶ/ር አወል ይህ ፎረም ዩኒቨርሲቲዎች ልምድ የሚለዋወጡበት ከመሆኑ ባሻገር በጋራ የሚሰሩበት እድል ይፈጥራል፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ልማት ላይ የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ ያስችላል፣ ለዚህም በጤና፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በዲጂታላይዜሽን እና በሌሎች ዘርፎች ላይ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የፎረሙ የቦርድ ሰብሳቢ እና የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አበበ ግርማ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ የፎረሙ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ታፈረ መላኩ ያለፉ አመታት የፎረሙ ስኬት እና ተግዳሮቶች ላይ ዳሰሳ አድርገዋል። ዩኒቨርሲቲዎች በሀገርና በአካባቢያቸው ሁለንተናዊ ልማት፣ ማህበረሰብ አገልግሎት፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ሌሎች ተለይተው በተሰጧቸው ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የተለያዩ ቁልፍ ንግግሮች ከተካሄዱ በኋላ የወሎ ዩኒቨርሲቲን ከምስረታ ጀምሮ አሁን ያለበት ድረስ (የ20 ዓመታት) ጉዞ የሚያሳይ አጭር ዶክመንታሪ ፊልም ለእይታ ቀርቧል።

ሁለት ቀን በቆየው በዚህ 24ኛው በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም 10 ዩኒቨርሲቲዎች እና አጋር ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ተሳተፊ ሲሆኑ የተለያዩ ጽሑፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፤ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችና ምክረሃሳቦችም ተቀምጠዋል።

በመጨረሻም የፎረሙ ተሳታፊዎች ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን በወሎ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ አሳረፈው ጉባኤው ተጠናቋል።

Scroll to Top