የወሎ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ የደን ሳይንስ ትምህርት ክፍል የሶስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ለማስጀመር የስርአተ ትምህርት ግምገማ አካሄደ

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ የደን ሳይንስ ትምህርት ክፍል በዘላቂ የደን አያያዝና አጠቃቀም /Sustainable Forest Management/ የትምህርት ዘርፍ የፍልስፍና ዶክትሬት ዲግሪ መርሃ ግብር ለማስጀመር የስርአተ ትምህርት ግምገማ አካሄደ።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ዳይሬክተርና የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶ/ር ቢኒያም ሽመልስ ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል የተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞችን እየከፈተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከነዚህም ውስጥ ይህ የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራም አንዱ ሲሆን እንደ ተግባር ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ስርአተ ትምህርቱ ተግባር ተኮር በሆነ መልኩ ተዘጋጅቶ የውስጥ ግምገማ ከተካሄደ በኋላ ለውጭ ግምገማ (External Review) መቅረቡንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ሀገራዊ ኢኮኖሚን ​​የሚደግፉ አስፈላጊ የስነ-ምህዳር አገልግሎቶችን የሚሰጡ የተለያዩ የደን ሀብቶች ያሏት በመሆኗ እነዚህን አስተዋፅኦዎች በመገንዘብ ሀገሪቱ የተለያዩ የደን ልማት ስልቶችን አዘጋጅታ ተግባራዊ እያደረገች እንደምትገኝ የገለጹት የወሎ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ጸጋዬ ጎበዜ ዩኒቨርሲቲው ጠንካራ የኢንዱስትሪ ትስስር ያለው የተግባር ዩኒቨርስቲ በመሆኑ በሃገራችን የተጀመረውን ተነሳሽነት ለመደገፍ ይህን የዶክትሬት ዲግሪ መርሃ ግብር ለመጀመር ማቀዱንም ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትርጉም ያለው ትብብር ለመፍጠር፣ ተፅዕኖ ያለው የምርምር ውጤት ለማመንጨት እና ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎችን ለማፍራት ይጠቅማል። በመሆኑም ይህ የሶስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር በሁለት ስፔሻሊቲ ፕሮግራሞች ተቀርጾ ለግምገማ ቀርቧል ብለዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የደን ሳይንስ ትምህርት ክፍል ሃላፊ ዶ/ር ሰለሞን ሙሉ በበኩላቸው ትምህርት ክፍሉ ከ2004 ዓ.ም ጀምር በመጀመሪያ ዲግሪ ከ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግማ የ2ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን በማስጀመር በርካታ ምሩቃን እያፈራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በእለቱ የስርአተ ትምህርቱ ገለጻ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ህትመት ስነምግባርና ስርጸት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ሰይድ ሙሄ የቀረበ ሲሆን የኢትዮጽያ የደን ልማት የደን ምርምር ክፍል ባልደረባ በሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር አደፍርስ ወርቁ እና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር መሃሪ አለባቸው እንዲሁም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የደን ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ በሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር አስማማው አለሙ ተገምግሟል።

በዚህ የግምገማ መርሃ ግብር ላይ የኮሌጅ ዲኖች፣ የትምህርት ክፍሉ መምህራንና ተመራማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን የቀረበውን ግምገማ ተከትሎ አስተያየቶች ተሰጥተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

Scroll to Top