ወሎ ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት፣ ም/ፕሬዚዳንቶች፣ የሶስቱም ግቢ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በተገኙበት የ2017 ዓ.ም የስራ አፈጻጸም እና የ2018 ዓ.ም እቅድ ግምገማ በደሴ ግቢ አካሄደ።
በመርኃ-ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አወል ሰኢድ በ2017 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው የተሰሩ አበይት ስራዎችን ሪፖርት አቅርበዋል። ከተግባር ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ መገለጫ ባህሪያትና ዩኒቨርሲቲን በእውቀት ከመምራት አንጻር በመቃኘት በዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ በምርምር፣ በቴክኖሎጅ ሽግግር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በፋይናንስ አጠቃቀም እንድሁም Key Performance Indicator_ KPIን ከመፈጸም አንጻር የተሰሩ ስራዎችን በዝርዝር አቅርበዋል።
በዚህም 2017 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲው የተሪሸሪ ኬርና ማስተማሪያ ሆስፒታል ግንባታና፣ በዋናው ግቢ የአስፓልት መንገድ ግንባታ የተጀመረበት፣ የአስተዳደር ሰራተኞች መዋቅርና፣ የህጻናት ማቆያ ግንባታ የተጠናቀቀበት፣ ዩኒቨርሲቲው ከ2016 ዓ.ም ከኦዲት ግኝት ነጻ የሆነበት፣ የላኮመልዛ ኢንተርፕራይዝ ለቦርድ ተጠሪ እንዲሆን የተደረገበት፣ ከ400 ሚሊየን ብር በላይ ከሃገር ውስጥ እና ከውጭ ሃገር አጋር ከካላት ጋር በተገኘ ትብብር የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በስኬት የተከናወኑበት፣ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር አባል መሆን የተቻለበትና ዩኒቨርሲቲው በያዛቸው ፕሮጀክቶች በዓአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ማግኘት የተቻለበት የስኬት አመት መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
የ2017 ዓ.ም የስራ አፈጻጸምን መነሻ በማድረግ ከመማር ማስተማር፣ ከምርምር እና ከማህበረሰብ አገልግሎት አንጻር በ2018 ዓ.ም ለመስራት በዕቅድ የተያዙ ዋና ዋና ተግባራትን፣ የክትትል፣ የድጋፍ፣ የግምገማና የሪፖርት ስርአቱን የተመለከተ ገለጻ በስትራቴጅክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ በአቶ አበባው ደምሴ ቀርቧል።
በቀረበው የስራ አፈጻጸም ሪፖርት እና እቅድ ላይ ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በ2017 ዓ.ም የስራ አፈጻጸም የታዩ ክፍተቶችን በመሙላት በ2018 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲውን በተሻለ አፈጻጸም ወደፊት ለማስኬድ ይጠቅማሉ የተባሉ ሃሳብ፣ አስተያየትና ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ቀርበው ከመድረክ ምላሽና አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል።
በተዘጋጀው መርኃ-ግብር ላይ በዩኒቨርሲቲው የተሰሩ ዋና ዋና መሰረተ-ልማቶችን መጎብኘት/የመስክ ምልከታ እና የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ተካሂዷል።