በወሎ ዩኒቨርሲቲ ለቤተ መጻህፍት ሰራተኞች ስልጠና ተሰጠ

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የደንበኞች አያያዝን፣ የጊዜና የሃብት አጠቃቀምን በተመለከተ በዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢና በልዕለ ህክምና ግቢ ለሚሰሩ 160 የሚሆኑ የቤተ መጻህፍት ሰራተኞች ስልጠና ተሰጠ።

ስልጠናው በዩኒቨርሲቲው በተሰራው የሰራተኞች መዋቅር መሰረት በክፍሉ አዲስ የተመደቡ ሰራተኞችን ጨምሮ ነባር ሰራተኞች በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ሳይንሳዊ እውቀት እንዲኖራቸው የሚያስገነዝብ ነው። የቤተ-መጻህፍት ሰራተኞች ተገልጋይ ተማሪዎችን እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው እንዲሁም ቡድን መሪዎችና የፈረቃ አስተባባሪዎች በስራቸው ያሉ ሰራተኞችን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀ ስልጠና እንደሆነ የቤተ መጻህፍት አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉነህ እንዳለው ተናግረዋል።

ስልጠናው በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማርኬቲንግ ማኔጅመንት መምህር በሆኑት በረዳት ፕሮፌሰር በእውቀቱ ዘለቀ ለ2 ተከታታይ ቀን የተሰጠ ሲሆን የቤተ መጻህፍቱን አፈጻጸም በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በጊዜና በሃብት አጠቃቀም ረገድ ውጤታማ ለማድረግ የሚረዱ ስልቶች ላይ ያተኮረ ነበር።

ሰልጣኞችም ስልጠናውን በንቃት የተከታተሉ ሲሆን ስልጠናው ጠቃሚና በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የነበራቸውን ግንዛቤ ያሰፋ እንደሆነ ገልጸዋል።

በስልጠናው መዝጊያ ላይ የተገኙት የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ፍቃዱ ቸኮል ስልጠናው ተማሪዎች ከተለያየ አካባቢ የሚመጡ ከመሆናቸው የተነሳ የሚያሳዩትን የተለያየ ባህሪ ተረድቶ በአግባቡ በማስተናገድ ውጤታማ ስራን ለመስራት ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን በመግለጽ አዘጋጆቹን አመስግነዋል።

ይህ ስልጠና በተመሳሳይ በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ግቢ ለሚሰሩ የቤተ መጻህፍት ሰራተኞች ቀጥሎ እንደሚሰጥ ተገልጿል።

Scroll to Top