ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአገር አቀፍ ደረጃ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በተደረገ የኮምፒዩተር ፕሮግራሚንግ ውድድር ሁለተኛ ደረጃ ወጣ፡፡
  January 04, 2021    News

በአገሪቱ ከሚገኙ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች መካከል ዘጠኙ በተሳተፉበት በዚህ ውድድር ላይ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ወሎ ሶፍት፣ ላሊበላ ሶፍት፣ ሀበሻ እና ቀለም ሜዳ በሚሉ አራት ምድቦች አማካኝነት አስራ ሁለት ተማሪዎች እንዲሳተፉ ያደረገ ሲሆን ውድድሩ ከአዳማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በቀጥታ ስርጭት ተካሂዷል፡፡ የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሶፍት ዌር ምህንድስና ትምህርት ክፍል ሃላፊ የሆኑት መ/ር ልዑል አይነኩሉ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ካላፈው አመት ጀምሮ በተመሳሳይ ዘውግ ውድድር ተሳትፎ ማድረግ እንደጀመረ አስታውሰው በወቅቱ አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ በአገር አቀፍ ደረጃ አሸናፊ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የውድደሩ ተሳትፎ አላማ ተማሪዎች በሶፍት ዌር ብልጽግና እና ፕሮግራሚንግ ብቁ እንዲሆኑ ማስቻል መሆኑን የሚናገሩት አቶ ልዑል ይህን እውን ለማድረግ እንደ ትምህርት ክፍል ከመምህራንና ሌሎች አካላት ጋር በጥምረት እየሰሩ እንደሚገኙ በመግለጽ በ21/04/2013 ዓ.ም የተደረገው የመጀመሪያ ዙር ውደድር በአገር አቀፍ ደረጃ ከተካሄደ በኋላ ያለፉት በየደረጃው በቀጠናዊና አለም አቀፋዊ ደረጃ እንደሚወዳደሩ አሳውቀዋል፡፡ አቶ ልዑል በዚህ ውድድር የተሳተፉ ተማሪዎች ብቁ እንዲሆኑ በተለያየ ጊዜ ልምምድ እንዲያደርጉ መደረጉን ገልጸው በቀጣይ ከአዳማ ሳይንስና ቴየክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ዋናው ካምፓኒ ከሚገኝበት ከኮሪያ ጋር ልምድ በመቅሰም ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን አልመው እንደሚሰሩ በመጠቆም ዩኒቨርሲቲው በእንደዚህ አይነት ውድድር ላይ ተሳትፎ እንዲያደርግ ቅንጅት ለፈጠሩ የትምህርት ክፍሉ መምህራን እና የተቋሙ አመራር አካላት ምስጋና ችረዋል፡፡ ማሰብ፣ መፍጠር እና መፈትሄ መስጠትን በሚጠይቀው በዚህ ውድድር በመስኩ የቀረቡትን ፈታኝ ጥያቄዎች በተሰጠው የጊዜ ገደብ በመጨረስ የውድድሩ አዘጋጅ አዳማ ሳይንስና ቴከኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ካሳተፋቸው አርባ አምስት ምድቦች ከፊት ተርታ በቅደም ተከተል ከተቀመጡጥ ዘጠኝ ምድቦች ቀጥሎ በአስረኛ ደረጃ ላይ ቀለም ሜዳ ምድብ የተቀመጠ ሲሆን አስካሁን ባለው የውድድሩ ሂደት እንደ ዩኒቨርሲቲ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡