በወሎ ዩኒቨርሲቲ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የተሰሩ ስራዎች ተጎበኙ ።
  November 16, 2020    News

በወሎ ዩኒቨርሲቲ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የተሰሩ ስራዎች ተጎበኙ ። ================= ወሎ ዩኒቨርሲቲ በደጋና ውርጫማ አካባቢ ተስማሚ የሆኑ የእንሰሳት መኖና የፍራፍሬ ዝርያዎችን ለማስፋፋት ዝርያ በማላመድ ላይ ይገኛል። በደቡብ ወሎ ደጋማ ቦታዎች እያጋጠመ ባለው የእንሰሳት የመኖ እጥረት ዩኒቨርሲቲው መፍትሄ ለመስጠት አንድ የአካባቢ ዝርያን ጨምሮ 8 (ስምንት) የስናር (የወበሎ) ዝርያዎችን ከ2011 ዓ ም ጀምሮ በደሴ ዙሪያ "ጉጉፍቱ" በማላመድ የተሻለውን ለማሰራጨት እየሰራ ነው። እነዚህ የመኖ ዝርያዎች በሳይንሳዊ መንገድ ከምርምር ማዕከል የወጡ ቢሆንም "ወደ ማላመድ የተገባው" የአካባቢውን የአየር ንብርትና መልከዓ ምድር ተቋቁም የእንሰሳት የመኖ ችግር ሊፈታ የሚችል ዝርያ ለማሰራጨት ነው ። ዩኒቨርሲቲው ለሁለተኛ ጊዜ (ዓመት) በደሴ ዙሪያ ወረዳ ጉጉፍቱ በማሳ እያላመደ ባለው የስናር (የወበሎ) ዝርያ ላይ አርሶ አደሮችን ያሳተፈ የመስክ ጉብኝት አካኈዷል። ይህንን የመስክ ጉብኝት የመሩት የወሎ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አሊ ሰይድ የመስክ ጉብኝቱ በአርሶ አደሮች የተሰጡ አስተያየቶችን፣ የተነሱ ጥያቄዎችንና ያሉ ስጋቶችን በማላመድ ወቅት ካገኘነው ሳይንሳዊ ውጤት ጋር በማዛመድ የተሻለውን ዝርያ ለይቶ ለማሰራጨት የሚያግዝ ነው ሲሉ ተናግረዋል። በዚህ የመስክ ጉብኝት የተሳተፉ የወሎ ዩንቨርሲቲ አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ የግብርና ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች በመስክ ተላምዶ ካዩት ስምንት የስናር መኖ ዝርያ መካከል የተሻለ ነው በማለት በራሳቸው ከመዘኑ በኋላ የሁሉም ስሜት የሳበ አንድ ዝርያ ቢሆን ብለው ጠቁመዋል። የወሎ ዩኒቨርስቲ በደቡብ ወሎ "ጉጉፍቱ" እያላመደ ካለው የመኖ ዝርያ በተጨማሪ በደሴ ከተማ በንብ ማነብና በደጋ ፍራፍሬ የሰራቸው ስራዎች ተጎብኝቷል። ዩኒቨርሲቲው በደሴ ከተማ አራዳና ሰኞ ገበያ በምግብ ዋስትና ታቅፈው በተራራ ልማት የተሰማሩ ኗሪዎችን ለማገዝ የሰጠው 2000 (ሁለት ሺ) የተሻሻለ የአፕል ዝርያ ተጎብኝቷል። በዚህም ጉብኝት በድጋፍ የተሰጠው የአፕል ዝርያ ከ90% በላይ መጽደቁን ለማረጋገጥ ተችሏል። የወሎ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፋሪስ ሀይሉ በዩኒቨርሲቲው የተሰጠው የአፕል ተክል ለውጤት በመብቃቱ በመደሰት ዩኒቨርሲቲው አሻራውን ሊያስቀምጥበትና ለውጥ ሊያመጣ በሚችል የስራ መስኮች ከተማ አስተዳደሩን የማገዝ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።