ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የራሱን አማካሪ ምክር ቤት አቋቋመ፡፡
  November 11, 2020    News

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የራሱን አማካሪ ምክር ቤት አቋቋመ፡፡ ሃዋሳ ላይ በነበረው ጉባኤ እንደተወሰነ በተገለጸው የተቋማት አማካሪ ምክር ቤት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው የትምህርትና ስልጠና ተቋማት የአማካሪ ምክር ቤት አሰራር ማዕቀፍ ላይ ተንተርሶ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች እና የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በተገኙበት ሰነዱ ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል፡፡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አጸደ ተፈራ የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሰላምና ጸጥታ ጉዳይ አርዓያ መሆኑን አውስተው ዩኒቨርሲቲው ለሚያከናውነው የመማር ማስተማር፣ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ ተሳትፎ ተግባራት የሚቋቋመው አማካሪ ምክር ቤት ሰላማዊ ከባቢን በመፍጠር ረገድ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያስችለዋል ብለዋል፡፡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተላከውን የአማካሪ ምክር ቤት የአሰራር ማዕቀፍ ሰነድ ለቤቱ አቅርበው ምክክር ተደርጎበታል፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የአማካሪ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶ/ር ከማል መሃመድዘይን የአደረጃጀት መዋቅሩን በማቅረብ ተጠሪነቱ ለተቀዋሙ ተቆጣጣሪ ቦርድ ሊሆን እንደሚገባ ምክረ ሃሳብ አቅርበው በቀጣይ ምክር ቤቱ የሚሰራበትን አግባብም ጠቁመዋል፡፡ የኮምቦልቻ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር መላኩ ታመነ በበኩላቸው ምክር ቤቱ ሰላምና ጸጥታ እንዲረጋገጥ ከማስቻሉም በላይ ተቋሙን ከማህበረሰቡ ጋር በማቀራረብ የሚሰሩ ስራዎችን ለማስተዋወቅ በር ይከፍታል ብለዋል፡፡ በዚህ የአማካሪ ምክር ቤት ምስረታ ውይይት ላይ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የወጣት ማህበር ተወካዮች፣ የጸጥታ አካላት እና ከልዩ ልዩ ተቋማት የተውጣጡ ግለሰቦች ጭምር የተገኙ ሲሆን ምክር ቤቱም ከሁሉም አካላት የተውጣጡ አባላት እንደሚኖሩት ታውቋል፡፡