ወሎ ዩኒቨርሲቲ የስልጠና ፕሮግራሙን ለማስቀጠል በሚያስችል አቋም ላይ መሆኑ ተገለጸ።
  October 12, 2020    News

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኔስተር በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተቋረጠውን የስልጠና ፕሮግራም ለማስቀጠል በዩኒቨርሲቲዎች እየተካሄደ ያለውን ቅድመ ዝግጅት ተንቀሳቅሶ ገምግሟል። በዚሁ መሰረት በወሎ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ቅድመ ዝግጅት ተንቀሳቅሶ ግምገማ ያካሄደው የሳይንስና ከፍተኛ ሚኔስተር ተቋሙ የኮሮና ወረርሽኝን እየተከላከለ መማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል በሚያስችል አቋም ላይ እንደሚገኝ ገልጿል። በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተገኘው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኔስተር ልዑክ በተማሪዎች የአገልግሎትና ስልጠና መስጫ (ምግብ ቤት፣ መኝታ ቤት፣ ክሊኒክ፣ ካፍቴሪያ፣ ሽንት ቤት፣ ሻወር ቤት፣ ቤተ መጽሀፍት፣ መማሪያ ክፍል፣ ቤተ ሙከራ ወዘተ) ምልከታ ካደረገ በኋላ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በተካሄደ ውይይት ተቋሙ በማንኛውም ሰዓት ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሰልጠን ይችላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ። በዚህ ውይይት የማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን የኮሮና ወረርሽኝ በመከላከል የስልጠና ፕሮግራሙን ለማስቀጠል ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኔስተር ባወጣው "የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማህበረሰብ አዋጅና መመሪያ" መሰረት ተቋሙ ቅድመ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ አብራርተዋል።