ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከኮምቦልቻ እና ደሴ ፖሊ ቲክኒክ ኮሌጆች ጋር በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ምክክር አደረገ፡፡
  August 21, 2020    News

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች በተገኙበት ከኮምቦልቻ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣ ከወይዘሮ ስህን ቴክኒክና ሙያ እና ከዞኑ መምሪያ ጋር ምክክር አድርጓል፡፡ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የመጡት ተወካዮች እና አጋር አካላት የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሜካኒካል፣ ሌዘርና ጋርመንት እንዲሁም የቴክስታይል ወርክ ሾፖችንና የተሰሩ ስራዎችን የጎበኙ ሲሆን በቀጣይ የቅንጅት አሰራር ላይ ትኩረት ያደረግ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከኮምቦልቻ እና ደሴ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችና በአቅራቢያው ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጋር በቅንጅት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን በኢንተርንሽፕ ፕሮግራም ተማሪዎች በጽንሰ ሃሳብ ያገኙትን እውቀት ኢንዱስትሪዎች ጋር የተግባር ልምምድ የሚያደርጉ ሲሆን በኤክስተርን ሽፕ ፕሮግራም ደግሞ መምህራን በክረምት ወራት ኢንዱስትሪዎች ጋር በመሆድ የአሰራር ችግሮችን በምርምር ይፈታሉ፡፡ የአካባቢን ጸጋ ለመጠቀም ስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ባደረገው በዚህ ውይይት የጋራ እቅድ፣ አደረጃጀትና አሰራር በመቀየስ ለአፈጻጻሙ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን የወቅቱ ችግር የሆነው የኮረና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሃርድ እና ሶፍት ዌር የስራዎች ፈጠራዎች እውቅና ተችሯቸዋል፡፡ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር የመጡት ተወካዮች በተሰራው ስራ የተሰማቸውን አድናቆት ገልጸው በመካከለኛና ከፍተኛ ደረጃ በሙያና በቀለም ትምህርት የሰለጠኑ ምሩቃን ስራ ፈጠራ ላይ እነዲሰማሩ የሚያበቃ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በትብብር መስራት ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ምክረ ሃሳብ ለግሰዋል፡፡ ወሎ ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲ፣ ኢንዱስትሪ እና ቴክኒክና ሙያ ትስስር ፕሮግራም በአከባቢው ካሉ ኢንዱስትሪዎችና ፖሊ ቴክኒኮች ጋር የሚሰራበትን ቅንጅታዊ አሰራር ተግባራዊ በማድረግ የተለያዩ አመርቂ ስራዎችን ከመስራቱም ባሻገር ከኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ደቡብ ወሎ ዞን እና የኦሮሞ ማህበረሰብ ልዩ ዞን ጋር በአራትዮሽ ፎረም ጨርቃ ጨርቅና አልባሳ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም በብረታብረት ኢንጂነሪንግ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባሻገር የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ስልጠናና የአቅም ግንባታ ተግባራት ላይ ትኩረት በማድረግ የስራ እድል ፈጠራ ላይ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ በውይይቱ ወቅት ተብራርቷል፡፡