በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት በኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ መምህራን በበጎ ፈቃድ የተሰሩ ሶፍትዌሮች ርክክብ ተካሂዷል፡፡
  August 21, 2020    News

ለደሴ ክላስተር የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ማዕከል የበለጸገ የሰርትፌኬሽንና ዶክመንቴሽን መተግበሪያ ሶፍት ዌር እና ለደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የዞኑን የባህልና የቱሪዝም ሃብቶች ለማስተዋወቅ የሚያግዝ ሶፍት ዌር ርክክብ ተካሂዷል፡፡ በኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ መምህራን በበጎ ፈቃድ የተሰሩት እነዚህ ሶፍት ዌሮች የተቋማቱን አሰራር ቀላል፣ ቀልጣፋና ዘመናዊ ከማድረጋቸውም በላይ የቁጥጥር ስርዓትን ለመዘርጋት እንደሚያመቹ የሁለቱም መስሪያ ቤቶች ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እውቅና ሰጥተዋል፡፡ የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ጽ/ቤት ሃላፊ ዶ/ር አሳምን አያሌው፣ የኢንፈርማቲክስ ኮሌጅ ዲን አቶ መልካሙ ጸጋዬ እና የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ጋሻው በቀለ ሶፍት ዌሮቹ በሂደት እንዳስፈላጊነቱ እየተሸሻሉ መሄድ የሚችሉ በመሆናቸው ተቋሙ አስፈላጊው እገዛ እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል፡፡ ሶፍት ዌሮቹን ያበለጸጉት መምህር ታደሰ ቢራራ እና ጓደኞቹ በበኩላቸው ሶፍት ዌሮቹን የሰሩት በተቋማቱ ችግር ላይ ተነስተው መሆኑን በመግለጽ በቀጣይ የቀረቡ አስተያየቶችን እንዳስፈላጊነቱ በማካተት ሁሉን አቀፍ አካታች ለማድረግና ስለአተገባበሩ ስልጠና መስጠት ላይ አልመው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ ተቋማቱም ዩኒቨርሲቲው ላደረገው የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምስጋና በመቸር ዘመኑ የመረጃ በመሆኑ የተሰሩላቸው ሶፍት ዌሮች መረጃን ለደንበኞችና ለባለ ድርሻ አካላት በቀላሉ ተደራሽ በማድረግ የአገልጎልት አሰጣጥ ጥራቱን ለማሳደግ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡