ወሎ ዩኒቨርሲቲ የህጻናት መቀንጨርን ለመከላከል የሚሰራውን ተግባር እንደሚያስቀጥል ገለጸ። ===================
  August 13, 2020    News

በህጻናት ላይ እየተከሰተ ያለውን መቀንጨር ለመከላከል ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከISD ዓለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በትብብር ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰራው የነበረውን ፕሮጀክት ለማስቀጠል የፕሮጀክት ትውውቅ አካሄዷል። በፕሮጀክት ትውውቁ የተገኙት የወሎ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገ/ም ፕሬዚዳንት ፋሪስ ሀይሉ (ዶ/ር) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአካል ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብም እየቀነጨረ ድንጋይ የሚወረውር ትውልድ እንዳይፈጠር በምርምር የተደገፍ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል። አያይዘውም ም/ፕሬዚዳንቱ ዩኒቨርሲቲ በደሴ ዙሪያ ወረዳ በአባሶና ቆላ ሙቴ ቀበሌዎች የጀመረውን የህጻናት መቀንጨር በ40% ለመቀነስ ከአስተሳሰብ ጀምሮ የእናቶችና ህጻናት የምግብ ስርዓት ለማሻሻል እንሰራለን ብለዋል። በውይይቱ ባለፉት ዓመታት በፕሮጀክቱ የተገኙ ስኬቶች እና በቀጣይ መሰራት የሚገባቸው አንኳር ነጥቦች ቀርበው ውይይት ከተካሄደባቸው በኋላ ፕሮጀክቱን ለቀጣይ ሁለት አመታት ለማስቀጠል የሚያስችል ውሳኔ ላይ ተደርሷል። በደቡብ ወሎ ዞን የደሴ ዙሪያ ወረዳ አባሶና ቆላ ሙቴ ቀበሌዎች ያለውን የህጻናት መቀንጨርን ለመከላከል የወሎ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ሁለት ዓመታት ስልጠናዎችን በመስጠት፣ የእንቁላል ዶሮ በማሰራጨትና የምግብ አውደ ርእይ በማካሄድ በእናቶችና ህጻናት የአመጋገብ ስርዓት ላይ ለውጥ ማምጣት ችሏል።