ወሎ ዩኒቨርሲቲ 4 መቶ አስራ ዘጠኝ የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን አስመረቀ።
  August 11, 2020    News

የወሎ ዩኒቨርሲቲው በ49 የስልጠና ፕሮግራሞች በመደበኛ፣ በኤክስቴንሽንና በክረምት ያሰለጠናቸውን የሁለተኛ ድግሪ ተማሪዎች አስመርቋል። ተቋሙ የድህረ- ምረቃ የስልጠና ፕሮግራሙን ለግማሽ ወሰነ ትምህርት በኦን ላየን (online) በመስጠት ተማሪዎችን ለማስመረቅ በቅቷል። የወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የሙያ ዘርፍ በሁለተኛ ድግሪ ያሰለጠናቸውን 350 ወንድ 69 ሴት በድምሩ 4 መቶ 19 ተመራቂዎችን ባሉበት በኦን ላየን ጭምር አስመርቋል። በምርቃቱ መልእክት ያስተላለፍት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አባተ ጌታሁን (ዶ/ር) ዓለም በኮረና ወረርሽኝ በተናወጠበትና የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሊት በተከሄደበት ዓመት መመረቃቸው ታሪካዊና ልዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል። አያይዘውም ፕሬዚዳንቱ ዩኒቨርሲቲው እቅዱን በአዲስ መልክ ሀገር በቀል እውቀቶችን ከምርምር ጋር በማቀናጀት ለውጥ በሚያስመዘግብ መልኩ ለመስራት የተዘጋጀ በመሆኑ ተመራቂዎች በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በሚሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ተግባራዊ ከማድረግ ጀምረው አዳዲስ ምርምሮችን ከዩኒቨርሲቲው ጋር የመስራት እድል ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል። በእለቱ የክብር እንግዳ የደሴ ከተማ ከንቲባ በሆኑት በአቶ አበበ ገ/መስቀል ለተመራቂዎች የስራ መመሪያ በመተላለፍ ፕሮግራሙ ተጠናቋል።