በተደረገልን የምግብ እና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ ከጎናችን የሚያስብልን ወገን እንዳለን ተገንዝበናል ሲሉ ድጋፉን ያገኙ የህብረተሰብ አካላት ገለጹ፡፡
  June 26, 2020    News

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ባደረገልን የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ ከጭንቀት አርፈናል በማለት በርክክቡ ወቅት የተገኙት ችግረኛ ወገኖችን ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቱ ሁለት መቶ ሃምሳ አንድ ሺህ ብር ወጭ አድርጎ የሃቢታት ሰፈር ስጋ ደዌ ተጠቂ ችግረኛ ማህበረሰብ ተወካይ እና የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ሃላፊ በተገኙበት የጤፍ ዱቄት፣ አተር ክክ፣ ፈሳሽ ሳሙናና የፊት መሸፈኛ ማስክ ርክክብ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን ከከተማው አስተዳደር እና ከሃቢታት ሰፈር የተውጣጡት ችግረኞች በአካል ተገኝተው ድርሻቸውን በተረከቡበት ወቅት ነበር ስሜታቸውን በእንባ ጭምር የገለጹት፡፡ ችግረኞቹ በአብዛኛው በእድሜ የገፉ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አዛውንቶች እና በአካል ጉዳት ሳቢያ ሰርተው መብላት የማይችሉ መሆናቸው ሳያንስ የኮረና ቫይረስ ወረርሽን እያደረሰባቸው ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ ያነጋገርናቸው ተረጅዎች “ባለብን የኑሮ ጫና ምክንያት ከቫይረሱ ይልቅ ረሃብ እንዳይገለን ነው ምንፈራው” በማለት ስጋታቸውን አጋርተው “ይህን ክፉ ወቅት አብረን መሻገር እንድንችል አቅም ያለቸው ሰዎች ከጎናችን ሊቆሙ ይገባል” በማለት ተማጽንዖ አሰምተዋል፡፡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት ቀደም ባሉት ጊዜያት ጭምር የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው በደሴ ከተማ አስተዳደርም ተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ከድር እንድሪስ በበኩላቸው ወሎ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሱቡ ውስጥ ዘልቆ በመግባት በእኔነት ስሜት የተለያዩ ማህበረሰባዊ ድጋፎችን በማድረግ አገራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸው ለሚደረገው ርብርብ ከተማ አስተዳደሩ እውቅና ይሰጣል ብለዋል፡፡