የባቲ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ተመረቀ።
  June 22, 2020    News

ከጅቡቲና አፋር ክልል የሚመጡ መንገደኞችን ለይቶ በማቆየት የኮረና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በባቲ የተቋቋመው የኳራንታይን ማእከል ተመርቋል። በወሎ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ የተቋቋመው የባቲ ለይቶ ማቆያ ማእከል ከሰኔ 8/2012 ዓ ም ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት ሁኗል። ማእከሉን የወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ የኦሮሚያ ብሄረሰብ ዞን አስተዳደር፣ የባቲ ወረዳና ከተማ አመራሮች፣ በጎ ፍቃደኞችና የሀገር ሽማግሌዎች በጋራ ተመርቋል። የቅኝት አምባ፣ የወሎየነት ተምሳሌትና የንግድ የመተላለፊያ አውድ ባቲ በታሪክ አጋጣሚ ከጅቡቲ አፋርን አቋርጠው በሚመጡ መንገደኞች የኮሮና ቫይረስ መተላለፊያ ኮሪደር ልትሆን ትችላለች የሚል ስጋት ተጭኖባታል። ከጅቡቲና አፋር ክልል እያቋረጡ የሚመጡ መንገደኞች ምርመራና ክትትል ሳይደርግላቸው ከመሀል ሀገር እንዳይገቡ ለማድረግ የለይቶ ማቆያ ማእከል በባቲ ማቋቋም ተገቢ መሆኑን በጥናት ለይተናል ያሉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን ባቲን ማዳን ወሎን፣ ሰሜን ሸዋን በአጠቃላይ ከቫይረስ ስርጭት ሀገርን መታደግ ነው ብለዋል። አያይዘውም ፕሬዚዳንቱ የኦሮሚያ ብሄረሰብ ዞንና የባቲ ከተማ አስተዳደር ዩኒቨርሲቲው የሰጣቸውን የለይቶ ማቆያ ቁሳቁስ በቀናት ውስጥ ሁሉን ነገር አዘጋጅተው ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረጋቸው የአመራሩ፣ የኮሚቴውና የማህበረሰቡ የቅንጅት ውጤት ነው ሲሉ ተናግረዋል። ወሎ ዩኒቨርሲቲ በደሴና ኮምቦልቻ ካቋቋመው የለይቶ ማቆያ ማእከል እኩል ግብአቶችንና ቁሳቁሶችን በማሟላት ሶስተኛው ማእከል እንድሆን የቻልነውን ሁሉ ለማድረግ እንሞክራለን ያለት የዩኒቨርሲቲው የአስ/ተማ/አገ/ም/ፕሬዚዳንት አማረ ምትኩ (ዶ/ር) ባቲ ከጅቡቲና አፋር የሚመጡ የከባድ መኪና ሹፌሮችና መንገደኞች መተላለፊያ ማእከል እንደመሆኗ መጠን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል። ወሎ ዩኒቨርሲቲ የወሎ ህዝብ አምባሳደርነቱን በተግባር እያስመሰከረ ነው ያሉት የኦሮሚያቭቤረሰብ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሀሰን ዩኒቨርሲቲው የዞናችንን አቅም መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎችን ከመስራትና ከማስተዋወቅ ጀምሮ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለከሚሴና ባቲ የለይቶ ማቆያ ማእከሎች ያደረገው ድጋፍ በታሪክ የትውልድ ቅብብሎሽ የሚዘከር ይሆናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ዩኒቨርሲቲው የባቲ ለይቶ ማቆያ ማእከልን ለማቋቋም ከ5 መቶ ሺ ብር በላይ የሚያወጡ የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን መዘገባችን ከአሁን በፊት የሚታወቅ ነው።