ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ችግረኛ የማህበረሰብ ክፍሎችና ለሃቢታት ሰፈር ስጋ ደዌ ተጠቂዎች የምግብ እና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ አደረገ፡፡
  June 20, 2020    News

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከአሁን ቀደምም በቋሚነት በተቋሙ የበጎ አድራጎት ክበብ አስተባባሪነት በኮምቦልቻ ከተማ ሃቢታት ሰፈር ለሚኖሩ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች በበአል ቀናት እርድ በማከናወን እና ልጆቻቸውን በማስተማር ጭምር ድጋፍ ሲያደርግላቸው የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስ ባደረሰባቸው የኢኮኖሚ ጫና ግምባር ቀደም ተጎጂ በመሆናቸው የምግብና ንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ አድርጎላቸዋል፡፡ ርክክቡ በተደረገበት ወቅት በስፍራው ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን ወሎ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በልዩ ልዩ መንገድ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው አሁን የገጠመን አገራዊ ችግር እስከሚያልፍ ድረስ ድጋፉ እንዳስፈላጊነቱ ተደራሽ የሚሆንበትን አሰራር እንከተላለን ብለዋል፡፡ የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር መላኩ ታመነ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በተቋሙ የተሰሩ ከንክኪ ነጻ የሆኑ የእጅ መታጠቢያ እና የፊት መሸፈኛ ማስኮችን በመስራት ለኮምቦልቻና ደሴ ከተማ እንዲሁም ለደቡብ ወሎና ለኦሮሞ አስተዳደር ልዩ ዞን ድጋፍ መደረጉን አስታውሰው በተመሳሳይ ለባቲ ለይቶ ማቆያ ማዕከል አስፈላጊው ግብዓት እንደተሟላ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር መላኩ በጊዜው የተከናወነው የምግብ እና ንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ ተቋሙ በእንዲህ አይነት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ወቅት ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች አጋርነታቸውን ለማሳየት መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ከድር እንድሪስ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅንጅት ለሚሰራቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፎች ምስጋና ችረው ካሁን ቀደም በክረምት ወራት ቤታቸው ለሚያፈስ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ሶስት ሽህ ቆርቆሮና ሚስማር ድጋፍ በማድረግ በበጎ አድራጎት ፈቃደኛ ወጣቶች እድሳት መካሄዱን አስታውሰው ለሃቢታት ሰፈር የስጋ ደዌ ተጠቂ የማህበር ክፍሎች ለባዕላት ቀን እርድ በማከናወንና በመማር ማስተማሩ መስክም የእውቀት ሽግግር በማድረግ ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ዛሬ በተደረገው ድጋፍ መቶ ከከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ ችግረኛ የከተማው ነዋሪዎችና ከአሁን በፊት በዩኒቨርሲቲው በተረፈ ምርት ድጋፍ በቋሚነት ሲረዱ ለነበሩ ስልሳ ስድስት የሃቢታት ሰፈር ስጋ ደዌ ተጠቂ ችግረኛ አባወራዎች አርባ ሁለት ኩንታል የጤፍ ዱቄት፣ አስራ ሰባት ኩንታል የአተር ክክ፣ መቶ ስልሳ ስድስት ባለ አምስት ሊትር ላርጎ እና መቶ ስልሳ ስድስት የፊት መሸፈኛ ማስክ የተበረከተ ሲሆን ድጋፉ በብር ሲገመት ሁለት መቶ ሃምሳ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ አስር ብር እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡