ወሎ ዩኒቨርሲቲ "ሀገር በቀል እውቀቶች ለሰላምና ለዴሞክራሲ ስርዓት ማሳለጫ" በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ አውደ-ጥናት እያካሄደ ነው።
  October 20, 2019    News

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከሳይንስና የከፍተኛ ት/ሚኔስተር፣ ከPDN፣ ከባህልንና ቱሪዝም ሚኔስተር ጋር በመተባበር 5ኛውን አለም አቀፍ የባህልና ኪነ-ጥበብ አውደ ጥናት እያካሄደ ነው። በዚህም አውደ ጥናት የወሎ የሀይማኖት አባቶች መገለጫና የትስስር ገመድ የሆኑት ቅኔና መንዙማ በሊቃው አባቶች ቀርበዋል። በአውደ ጥናቱ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/አባተ ጌታሁን እንግዶች እንኳን በሰላም መጣችሁ በማለት ወሎ ለአራቱ ቅኝቶች መነሻ መንፈስን የሚያድሱ ቅኔዎች የሚዘረፉበት መንዙማዎች የሚንቆረቆርበት በሀገር በቀል እውቀቶች ስብጥር የተሞላ የባህልና የታሪክ አውድማ ነው ሲሉ ተናግረዋል። አያይዘውም ፕሬዚዳንቱ በወሎ ያሉ ሀገር በቀል እውቀቶች በህዝቦች መካከል አንድነትንና አብሮነትን በማስተማር የኢትዮጵያውያንን የመደመር ፍልስፍና የሚያጠናክሩ እሴቶች በመሆናቸው በጥናት እያስደገፉ ከጥቅም እንድውሉ የማድረግ ግደታ አለብን ሲሉ ገልጸዋል። በአውደ ጥናቱ ቁልፍ መልእክት ያስተላለፉት በሳይንስና የከፍተኛ ት/ሚኔስተር የከፍተኛ ት/ሚኔተር ደኤታ ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ የክቡር ጠ/ሚኔስተር ዶ/ር አብይ አህመድ "መደመር" የሚለው መጽሀፍ እየተመረቀ ባለበት እለት ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀቶች ለሰላምና ለዴሞክራሲ ማሳለጫ እንድያግዙ አውደ ጥናት መካሄዱ በሀገራችን እያጋጠመ ያለውን የማህበራዊ ግንኙነት ወለምታ አሽተው የሚያስተካክሉ ካስማና ማገር በመሆናቸው ተጠናክረው እንድቀጥሉ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። በዚህ አውደ ጥናት በሀይማኖት አባቶች አንድነትን፣ አብሮነትንና ፍቅርን የሚያስተምሩ ቅኔዎች በአማረኛ ፣ በግእዝና በእንጊሊዘኛ ቋንቋዎች ተዘርፈዋል። በተመሳሳይ መልኩ የአድማጭን ስሜን ቆንጥጦ የያዘው የወሎ መንዙማ በታዋቂው ሸህ መሀመድ አወል ተንቆርቁሯል። በ5ኛው ዓለም አቀፍ የባህልና ኪነ-ጥበብ አውደ ጥናት ከ16 በላይ ሀገር በቀል እውቀቶች ላይ ያተኮሩ ጥናቶች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።