ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከቃሉ ወረዳና የቀበሌ አጋር አካላት ጋር በሀርቡ የእርሻ መሬት አጠቃቀምና በቀጣይ በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ የጋራ ምክክር አደረገ፡፡
  June 20, 2022    News

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከቃሉ ወረዳና የቀበሌ አጋር አካላት ጋር በሀርቡ የእርሻ መሬት አጠቃቀምና በቀጣይ በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ የጋራ ምክክር አደረገ፡፡ ----------------------------------------------------------- በቃሉ ወረዳ ቀበሌ 33 ጠከኬ ላይ ለምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራ በሚል 11 ሄክታር መሬት የተረከበው ወሎ ዩኒቨርሲቲ ቦታውን በማልማት ሂደት ባጋጠሙ ችግሮች እና በቀጣይ ሊሰሩ በታቀዱ ተግባራት ዙሪያ ከወረዳው ከተውጣጡ ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ምክክር አድርጓል፡፡ የቃሉ ወረዳ ም/ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን አህመድ በመክፈቻ ንግግራቸው ወሎ ዩኒቨርሲቲ የወሰደውን ቦታ በማልማት ረገድ ትልቅ አቅም እንዳለው ገልጸው በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት በሚያደርገው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ልማትን በማረጋገጥና የግብርና ኤክስቴንሽን የምርምር ስራዎችን በማጎልበት የተሻለ የእርሻ የምርምር ተቋም በማድረግ አካባቢው ጭምር ተጠቃሚ የሚሆንባቸውን ማሳያዎችን ጠቅሰዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ ሁለት ወረቀቶች የቀረቡ ሲሆን በላኮመንዛ ኢንተርፕራይዝ በቀረበው በመጀመሪያው ሪፖርት ላይ በቦታው ላይ እስካሁን የተሰሩ ስራዎች እና ያጋጠሙ ችግሮች ተዳሰዋል፡፡ በዚህም በሰብል ልማት፣ ቴክኖሎጅ ሽግግር እና የማህበረሰብ አገልጎሎት ስራዎች የተቃኙ ሲሆን በሌላ በኩል የመንገድ፣ የድንበር መግፋት፣ የጎርፍ አደጋ፣ የመስኖ አማራጭ አለመኖር እና ሌሎች ምክንያቶች በችግር ተነስተው የመፍትሄ ሃሳቦችም ተመላክተዋል፡፡ በግብርና ኮሌጅ በቀረበው ሪፖርት ደግሞ በቀጣይ በመሬቱ ላይ ሊከናወኑ የታቀዱ ተግባራት የቀረበ ሲሆን ይህንን ተከትሎ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱም ወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ ግብርና ኮሌጅ እና የቃሉ ማህበረሰብ በቅንጅት ለውጥ ተኮር ተግባራትን ለማከናወን አልመው እንደሚንቀሳቀሱ የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን ማህበረሰቡ ላሳየው ትዕግስት፣ ቀናነትና ዘግጁነት እንዲሁም ወረዳው ስራውን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ፈጥኖ ወደ ልማት ለመግባት ላሳየው ቀርጠኝነት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች እውቅና ሰጥተዋል፡፡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነው መሬቱ ላይ የተግባር ልምምድ ስራዎችን በማከናወን ለመማር ማስተማር፣ ምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራት እንደሚከናወንበት ገልጸው ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጂ በመታገዝ ምርጥ ዘርን በማውጣትና በማላመድ እንዲሁም ዘመናዊ አሰራርን በመከተል ምርትና ምርታማነትን አሳድጎ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንደሆን በሚቻልበት አግባብ ላይ ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ዶ/ር መንገሻ አያይዘው በወረዳው ላሉ የተለያዩ የማህበረሰብ ከፍሎች ስልጠና እና የትምህርት እድል በማመቻቸት ዘርፉ በሳይንሳዊ አሰራሮች እንደደገፍ ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ሙሉጌታ ዳውድ እንደዘገበው