ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ወሎ በጃራ የመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የምግብ ድጋፍ አደረገ።
  June 20, 2022    News

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ወሎ በጃራ የመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የምግብ ድጋፍ አደረገ። ==================== በህወሀት መራሹ የጥፋት ቡድን ከፍተኛ ውድመት የደረሰበት የወሎ ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ወሎ በጃራ የመጠለያ ጣቢያ በምግብ እጥረት ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ህይወት ለመታደግ ቅድሚያ በመስጠት ድጋፍ አድርጓል። ዩኒቨርሲቲው ድጋፉን ያደረገው በማንነታቸው ምክንያት በህወሀት የጥፋት ቡድን ከቤት ንብረታቸው ከራያ ቆቦ፣ አላማጣ፣ ከኮረምና ራያ ባላ ለተፈናቀሉ ወገኖች ነው። ወሎ ዩኒቨርሲቲ በህወሀት በደረሰበት ውድመት የቤተ ሙከራ ቁሳቁሶችን ጨምሮ በርካታ ቁሳቁሶችን የማሟላት አስገዳጂ ጉዳዮች ቢኖሩበትም በሰሜን ወሎ በጃራ መጠለያ ጣቢያ ያሉ ተፈናቃዮችን ህይወት ለመታደግ ለሰበዓዊ ድጋፍ ቅድሚያ ሰጥተናል ያሉት የድጋፉ አስተባባሪና የወሎ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ብረሃኑ አስማሜ ዩኒቨርሲቲው 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ 350 ኩንታል ነጭ ዱቄት ለተፈናቃዮች እንዳስረከቡ ገልጸዋል። እንደዳይሬክተሩ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው የፈረሱበትን ህንጻዎች መገንባት፣ የቤተ ሙከራና የICT መሰረት ልማቶችን ማሟላት እያለበት ቅድሚያ ለሰው ልጆች ለመስጠት ሲል ካለችው ውስን በጀት ላይ ቀንሶ ያደረገው ተግባር በመሆኑ ሌሎች ተቋማትም ለሰብዓዊነት ቅድሚያ እንድሰጡ አሳስበዋል። ወሎ ዩኒቨርሲቲ በህወሀት የጥፋት ቡድን ከደረሰበት ውድመት በማገገም በሰሜን ወሎ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ያደረገው ድጋፍ ለሰው ልጅ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ያስመሰከረበት መልካም ተግባር ነው ያሉት የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ፋሲል አረጋ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የወሎ ዩኒቨርሲቲን መልካም ተግባር ተከትለው ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉ ያላቸውም ተስፋ ገልጸዋል። በመጠለያው ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች በበኩላቸው ከፍተኛ የሆነ የምግብ፣ የመድሀኒትና የወጥ እህል እጥረት እንዳለባቸው በመግልጽ የወሎ ዩኒቨርሲቲን ተከትለው ሌሎች ተቋማት የአቅማቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። በመጨረሻም የሀብሩ ወረዳ የ024 ቀበሌ አስተዳደርና የጦር ጀኔራል የሆኑት ሀሰን ከረሙ ጦርነቱ የቀበሌየን ህዝብ ጨምሮ አብዛሀኛውን የሰሜን ወሎ ወረዳና ቀበሌዎች ለረሃብ ዳርጎ ያለፍ መጥፎ አጋጣሚ ቢሆንም በጃራ መጠለያ ጣቢያ ያለው ግን የከፋ በመሆኑ ወሎን ለመታደግ እንረባረብ ብለዋል። አያይዘውም ጀኔራል ሀሰን ከረሙ በጦርነቱ ሰዓት የነበረው መረባረብና መደጋገፍ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ የቆመ በመሆኑ ህዝብ በረሃብ እየተቃጠለ ስለሆነ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንድያደርጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በጃራ የመጠለያ ጣቢያ ከ30 ሺ በላይ ተፈናቃዮች ሲኖሩ አብዛሀኛዎቹ ህጻናትና ሴቶች ናቸው።