ወሎ ዩኒቨርስቲ ከ39 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ በተንታ አትሌቲክስ ማዕከል ተተኪ ስፖርተኞችን እያፈራ መኾኑን ገለጸ፡፡
  May 03, 2022    News

ወሎ ዩኒቨርስቲ ከ39 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ በተንታ አትሌቲክስ ማዕከል ተተኪ ስፖርተኞችን እያፈራ መኾኑን ገለጸ፡፡ ደሴ: ሚያዝያ 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ዩኒቨርስቲዉ በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ድጋፍ ከሚያደርግላቸዉ ተቋማት መካከል የተንታ አትሌቲክስ ማዕከል አንዱ ነዉ፡፡ በአኹኑ ወቅት ሃምሳ የሚሆኑ ታዳጊ አትሌቶች በማዕከሉ በመሰልጠን ላይ ይገኛሉ፡፡ አትሌት ፂዮን አበበ በቅርብ አሰላ ከተማ ላይ በተካሄደ ሀገር አቀፍ ዉድድር የወርቅ ሜዳልያ በማገኘት በ3 ሺህ ሜትር ሀገሯን የመወከል እድል አግኝታ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እያደረገች መኾኑን ገልጻለች፡፡ በማዕከሉ በመሰልጠኗም ዉጤታማ እንድትኾን እንዳደረጋት ተናግራለች፡፡ አትሌት ፂዮንን ጨምሮ በተንታ አትሌቲክስ ማዕከል የሚሰለጥኑት አትሌቶች ወሎ ዩኒቨርሲቲ ህልማችንን እዉን እንድናደርግ ስለረዳን እናመሰግናል ብለዋል፡፡ ወደፊትም የሀገራቸዉን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ ብሎ እንዲዉለበለብ በትጋት ልምምድ እየሠሩ መኾናቸዉን ተናግረዋል፡፡ በአትሌቲክስ ማዕከሉ የመካከለኛ ርቀት አሰልጣኝ ኃይሉ አማረ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማዕከሉ ለክልሉ ብሎም ለሀገር ኩራት የሆኑ አትሌቶችን እያፈራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ አካዳሚ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ተገኝ ተሰማ ዩኒቨርሲቲዉ ከ39 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ለተንታ አትሌቲክስ ማዕከል ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የአምስት ዓመታት ፕሮጀክት በመቅረፅም ታዳጊ አትሌቶችን ዉጤታማ ለማድረግ እተሠራ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡