በአሸባሪው ህወሃት ውድመት የደረሰበትን ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከማዕድን ሚኒስቴርና በስሩ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ጅኦሎጅካል ሰርቬ ኢኒስቲትዩት ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ ማግኘቱን ገለጸ::
  April 26, 2022    News

በአሸባሪው ህወሃት ውድመት የደረሰበትን ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከማዕድን ሚኒስቴርና በስሩ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ጅኦሎጅካል ሰርቬ ኢኒስቲትዩት ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ ማግኘቱን ገለጸ:: ድጋፉ ከአዲስ አበባ ወደ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ሲገባ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት ዩኒቨርሲቲው ዳግም ስራ እንዳይጀምር አድርጎ ዉድመት አድርሶበታል፡፡ ይሁን እንጅ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብና የተለያዩ ተቋማትንበ በማስተባበር መልሶ እያቋቋመ ዳግም ስራ እንዲጀምር አድርጎታል ብለዋል፡፡ የተጀመረውን የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠልና ለማጠናከር ማዕድን ሚኒስቴርና በስሩ የሚገኙ የኢትዮጵያ ጅኦሎጅካል ሰርቬ ኢኒስቲትዩት ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገውልን ዛሬ ወደ ዩኒቨርሲቲያችን ማስገባት ችለናል ብለዋል፡፡ እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ ድጋፉ ወንበር፣ ጠረጼዛና የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶችንና የተለያዩ ስቴሽነሪዎችን ያካተተ ነው፡፡ የተደረገው ድጋፍ የተሻለ ትምህርት ለተማሪዎች ለመስጠት እንደሚያግዝ ጠቁመው ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከማዕድን ሚኒስተር ጋር በጋራና በትብብር እንደሚሰራ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ በተለይ በዩኒቭርሲቲው ሚገኘውን የጅኦሎጅ ዲፓርትመንት ከሚንስትር መስሪያ ቤቱ ጋር በማስተሳሰር ሰፊ የማህበረሰብ አገልግሎት ተግባር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውን መልሶ ለማቋቋም ሀብት አፈላላጊ ኮምቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኮሚቴው አባልና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎትና ስልጠና ዳሬክተር ደክተር ጌታቸው ጉግሳ ናቸው፡፡ በቅንጅት መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ህብረተሰቡና ተቋማት እየደገፉ በመሆኑ በፍጥነት ዩኒቨርሲቲው እየተቋቋመ መሆኑን ጠቁመው የዛሬው ድጋፍም የዚሁ አንድ አካል ነው ብለዋል፡፡