ወሎ ዩኒቨርሲቲ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በተቋሙ በፈጸመው ዝርፊያና ውድመት ዙሪያ ትኩረት ያደረገ የምርምር አውደ ጥናት አካሄደ ::
  April 12, 2022    News

ወሎ ዩኒቨርሲቲ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በተቋሙ በፈጸመው ዝርፊያና ውድመት ዙሪያ ትኩረት ያደረገ የምርምር አውደ ጥናት አካሄደ :: ========================== ወሎ ዩኒቨርሲቲ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት አነሳሽነት በተቋሙ አጥኝዎች በአሸባሪ ቡድኑ የደረሰውን መጠነ ሰፊ ጉዳትና ውድመት ለተወሰነ ጊዜ ምርምር ሲያደርግ ቆይቶ ጥናቱን ይፋ የሚያደርግ አውደ ጥናት አካሂዷል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፋሪስ ሃይሉ በመክፈቻ ንግግራቸው የምርምር አውደ ጥናቱን አላማ ያስረዱ ሲሆን በዝግጅቱ ለታደሙ አካላትም እውቅና ሰጥተዋል፡፡ ኮምቦልቻ ከተማ በተካሄደው በዚህ የምርምር አውደ ጥናት ላይ ዶ/ር ፋሪስ ሃይሉ በአካባቢው ለተፈጠረው አሁናዊ መረጋጋት የጸጥታ አካላት ምስጋና ይገባቸዋል በማለት አሸባሪው የህወሃት ቡድን ለብዙ አስርት አመታት ያደረሰውን አገራዊ ጉዳት ቃኝተዋል፡፡ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በወሎ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር አወል ሰይድ በበኩላቸው ስለመማር ማስተማር ስራ በመዳሰስ ምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራት እውቀትና ቴክኖሎጂ በማስረጽ ሁለንተናዊ እድገትን እንደሚያፍጥን አጽንዖት ሰጥተዋል አያይዘውም ዩኒቨርሲቲ የተጣለበትን ሃላፊነት እንዳይወጣ ከተደረገ የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት አስምረውበታል፡፡ ዶ/ር አወል አውደ ጥናቱ ችግሮችን በመዳሰስ የመፍትሄ መንገዶችን ለመቃኝት እድል እንደሚሰጥ ያላቸውን እምነት ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በእለቱ ቁልፍ ንግግር ያደረጉት ተጋባዥ እንግዳ ፕሮፌሰር ሹመት ስሻኝ "የኢትዮያ ፈተናዎችና የድሏ ሚስጢር" በሚል ርዕስ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በዩኒቨርሲቲው አጥኝ ቡድን በወረራው ወቅት ስለነበረው ከበባዊ ገጽታ፣ በዩኒቨርሲቲው ስለፈጸመው ውድመትና ዝርፊያ እንዲሁም በትምህርት ተቋም የተፈጸመው የጦርን ወንጀልን የተመለከቱ ሶስት የጥናት ወረቀቶች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን የመፍትሄ ሃሳቦችም ተመላክተዋል፡፡ በምርምር አውደ ጥናቱ ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የዩቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ጉዳይ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አማረ ምትኩ በተካሄደው ውይይት ጠቃሚ ሃሳቦች መሰንዘራቸውን ገልጸው ተቋሙ በቀጣይ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ትልቅ ግብዓት ናቸው ብለዋል፡፡ Reported by Mulugeta Dawud (Kombolcha campus PR Team leader)