የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ወሎ ዪኒቨርሲቲን መልሶ ለማቋቋም የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
  April 10, 2022    News

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ወሎ ዪኒቨርሲቲን መልሶ ለማቋቋም የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ። ============== ወሎ ዩኒቨርሲቲን መልሶ በማቋቋም ወደ ስራ እንድገባ የሚያግዙ ድጋፎች ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እየተደረገለት ይገኛል። ዩኒቨርሲቲው እያደረገ ያለውን መልሶ የመቋቋም ጥረት ለማገዝ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኮምፒዩተር፣ የላፕቶፕ፣ የቢሮና የቤተ ሙከራ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል። ድጋፉን በአካል ለወሎ ዩኒቨርሲቲ ያስረከቡት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ ተቋሙን ወደ ነበረበት ለመመለስ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው የመጀመሪያውን ዙር ድጋፍ እንዳደረገ ገልጸዋል። ወራሪው ሀይል ተሸንፎ አካባቢውን ለቆ እንደወጣ በዩኒቨርሲቲው በመገኘት ጉብኝት በማካሄድ የደረሰውን ውድመት በአይናችን ተመልክተናል ያሉት ሚኔስትሩ ተቋሙን መልሶ ለመገንባት የሁሉም አካላትን ርብርብ ይጠይቃል ሲሉ ተናግረዋል። አያይዘውም ሚኒስትሩ ተቋሙ የደረሰበትን የቴክኖሎጅ ውድመት መልሶ ለመገንባት ሚኔስቴር መስሪያ ቤት በቴክኖሎጅና በስልጠና በትብብር እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል። ድጋፉን የተረከቡት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያደረገላቸውን ድጋፍ በማመስገን ከተለያዩ ተቋማት በተደረገላቸው የኮምፒዩተርና የቁሳቁስ ድጋፍ ወድሞ የነበረውን የኤሌክትሮኒክስ ላይብራሪ መልሶ በማደራጀት የስልጠና ፕሮግራሙን ለማስቀጠል እንዳገዛቸው ገልጸዋል። በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ በመጀመሪያው ምእራፍ ተቋሙን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴ ከዩኒቨርሲቲዎችና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተገኘው ድጋፍ አይነተኛ ሚና መጨዋቱን በመግለጽ ወደፊት ዩኒቨርሲቲው በሚያካሄደው የመልሶ ግንባታና የማደራጀት ምዕራፍ ላይ ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።