በወሎ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን፣ ማርች 8፣ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ፡፡
  April 06, 2022    News

በወሎ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን፣ ማርች 8፣ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ፡፡ ዓለማቀፍ የሴቶች ቀን “ማርች 8” በአለም ለ111ኛ፣ በኢትዮጵያ ለ46ኛ ጊዜ "እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ" በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት በወሎ ዩኒቨርሲቲ በሴቶችና ህጻናት ዳይሬክተር አስተባባሪነት በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ በዚህም የዩኒቨርሲቲው የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ተ/ዳይሬክተር ወ/ሮ የሸወርቅ አሰፋ የበአሉን አከባበር ታሪካዊ አመጣጡን አስመልከቶ ገለጻ አቅርበው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አማረ ምትኩ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት ሴቶች ይህን በአል ስታከብሩ በርካታ ዓለማቀፋዊና ሀገራዊ ፈታኝ ክስተቶችን አሳልፋችሁ /ኮሮና እና የእርስ በርስ ጠርነት/ በመሆኑ ያለፉትን ታሪኮች በማንሳት ብቻ ሳይሆን በርካታ ያልተፈቱ ጥያቄዎችን የምታስተጋቡበትና እንዲፈታ የምትጥሩበት መድረክ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ ልማትና አለማቀፍ ትብብር ም/ፐሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር አጸደ ተፈራ በቁልፍ ንግግራቸው እንዳስተላለፉት ማርች 8ን ስናከብር የአውሮፓውያንን ባህልና ክስተቶችን በማስተጋባት የምናከብርበትን ሁኔታ ትተን ከ 111 ዓመት በፊት የነበሩ የኛዎቹን ኢትዮጵያውያን ሴቶች የእነ እቴጌ ጣይቱንና መሰሎችን የሴት ጀግኖች በማውሳት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ሴቶችን ወደሚፈለገው ደረጃና የስልጣን እርከን ለማምጣት ሁላችንም በተሰማራንበት መስክ አርአያ ሆነን መገኘት አለብን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በዕለቱም "የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና በጾታዊ እኩልነት" በሚል ርዕስ በማህበራዊና ሰብአዊ ሳይንስ ኮሌጅ የሶሽዮሎጅ ትምህርት ክፍል መምህርት የሆኑት ረ/ፕሮፌሰር ፋጡማ አብዱ የፓናል ውይይት መነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ዶ/ር አቻምየለሽ አማረ እና ረ/ፕሮፌሰር የሽመቤት አሊ ለበአሉ ታዳሚዎች የማነቃቂያ ንግግር አድርገዋል፡፡