ሰመራ ዩኒቨርሲቲ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው ጦርነት ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ አደረገ። =================
  October 13, 2021    News

ሰመራ ዩኒቨርሲቲ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው ጦርነት ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ አደረገ። =================== የወሎ ዩኒቨርሲቲ ያደረገውን የድጋፍ ጥሪ ተከትሎ በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በደሴና ኮምቦልቻ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ። የራሱ ከፍተኛ ችግር እያለበት ይህንን የድጋፍ ጥሪ የተቀበለው የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከሰሜን ወሎና ከዋግምህራ ዞን ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል። ድጋፉን ያስረከቡት የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አቡበክር ያሲን የአማራ ህዝብ ችግር የአፋር ህዝብ ችግር ነው የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከህዝብ ጎን መሆኑን ለማረጋገጥ ያደረገው ድጋፍ ነው ሲሉ ገልጸዋል። ጦርነቱ የአማራን ህዝብ ብቻ ሳይሆን የአፋርንም ህዝብ ያጠቃ ነው ያሉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተርና የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ጌታቸው ጉግሳ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ያደረገው ድጋፍ የወሎ እና የአፋርን ህዝብ የቆየ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ያሳየ መልካም ተግባር ነው ብለዋል። አያይዘውም ዳይሬክተሩ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ በአፋር ህዝብ ላይ የተከሰተውን መፈናቀልና ስደት ከማረጋጋት ጎን ለጎን የወሎ ዩኒቨርሲቲን የድጋፍ ጥሪ ተቀብሎ የሰጠው ምላሽ ለአማራ ህዝብ ያለውን አንድነት ያሳየ ተግባር ነው ሲሉ ተናግረዋል። የሰመራ ዩኒቨርሲቲ በደሴ እና ኮምቦልቻ ለተፈናቀሉ ወገኖች ያደረገውን የማገዶ እንጨት፣ የምግብ፣ የአልባሳትና የፍራሽ ድጋፍ ለወሎ ዩኒቨርሲቲ አስረክቧል።