ወሎ ዩኒቨርሲቲ በአውሮፓ ህብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በግብርናው ዘርፍ ያከናወነውን የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት መኖ ልማት ሰርቶ ማሳያ የምርምር ስራዎችን በአፋር ክልል ጭፍራ ወረዳ የመስክ ምልከታ አካሂዷል፡፡ ›››››››››››››››››››››››››››++++++++++++++++++++››››››››››››››››››››››››››
  September 29, 2021    News

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በአውሮፓ ህብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በግብርናው ዘርፍ ያከናወነውን የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት መኖ ልማት ሰርቶ ማሳያ የምርምር ስራዎችን በአፋር ክልል ጭፍራ ወረዳ የመስክ ምልከታ አካሂዷል፡፡ ›››››››››››››››››››››››››››++++++++++++++++++++›››››››››››››››››››››››››› ወሎ ዩኒቨርሲቲ ICRISAT/International Crops Research Institute For The Semi-Arid Tropics/ ከተባለ አለማቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በተለይም አርብቶ አደሩንና ከፊል አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ በምርምር የታገዘ የተለያዩ ለአየር ንብረቱ ተስማሚ የሆኑና በምርታማነታቸው የተረጋገጠ በንጥረ ምግብነት ይዘታቸው የተሻሉ በአይረንና ዚንክ የበለጸጉና መቀንጨርን የሚከላከሉ፣ የሰብል ዝርያዎችን ( የበቆሎ፣የማሽላ፣የጤፍ፣የማሾና የዳጉሳ )፤ በተጨማሪም የእንስሳት መኖ( ላብላበ፣የዝሆኔ ሳርና የላም አተር ) በተግባር በቦታው ያከናወነው የምርምር ሙከራ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በቦታው የተገኘው የምልከታ ቡድንና በሙከራው ላይ የተሳተፉ ከፊል አርሶና አርብቶ አደሮች አረጋግጠዋል፡፡ በአፋር ክልል ጭፍራ ወረዳ የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ወግሪስ ሀፋ በመክፈቻ ንግግራቸው አንደገለጹት ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር የአካባቢውን ህዝብ ለመጥቀም የሚያከናውነው ተግባር የሚበረታታና የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም ለሙከራ የሚሆን 20.9 ሄክታር ላይ የለማው ሰብል ለቀጣይ ተስፋ የሚሆንና ከፊል አርሶና አርብቶ አደሮችን በትኩረት ወደሰብል ምርት እንዲገቡ ያነቃቃ ነው ብለዋል፡፡ በወረዳው በርካታ ለሰብል ልማት የሚሆን የእርሻ መሬት ቢኖርም ገና ያልተሰራበት መሆኑን ጠቁመው ከወሎ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች አጋር አካላት ጋር ተቀናጅተን ህብረተሰቡን በምግብ ራሱን ከመቻል ባለፈ ለገበያ የሚያቀርብበትን ሁኔታ እንፈጥራለን በማለት ገልጸዋል፡፡ በግብርና ኮሌጅ መምህር ተመራማሪና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሁነኛው አበበ እና በኮሌጁ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አደም መሀመድ ባደረጉት የጉብኝት ገለጻ ከቦታው የአየር ንብረት አኳያ ሊላመዱ የሚችሉ በፍጥነት ሊደርሱና ውጤታማነታቸው በጥናትና ምርምር የተረጋገጡ የሰብልና የእንስሳት መኖ ዝርያወች ለከፊል አርሶና አርብቶ አደሩ ተሰራጭተው እየለሙ መሆኑን አብራርተው በጉብኝቱ እንዳየነውም ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ በመሆኑ ቀጣይ ወደሌሎች አካባቢዎች ሊሰፋ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፋሪስ ኃይሉ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከሚያከናውነው የመማር ማስተማር ጎን ለጎን በምርምር ስራዎች በመታገዝ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ ከዚህም መካከል በአፋር ክልል ጭፍራ ወረዳ ከፊል አርብቶና አርሶ አደሩን ምርታማና ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ የሰብልና የእንስሳት መኖ ዝርያዎችን ከማቅረብ ባለፈ የባለሙያ ከትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አካባቢው በረሃማና ርጥበት አጠር በመሆኑ ድርቅን መቋቋም የሚችሉ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ፣ምርታማ የሆኑ፣ በንጥረ ምግብነት ይዘታቸው የተሻሉ በአይረንና ዚንክ የበለጸጉና መቀንጨርን የሚከላከሉ፣ በሽታን መቋቋም የሚችሉና ለአየር ንብረቱ ተስማሚ የሆኑ ሰብሎችን በማላመድ ህብረተሰቡ በግብርና ዘርፉ ተጠቃሚ እዲሆን እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው አካባቢውን በስፋት እንዲለማ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዘግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡