በምስራቅ አማራ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በወሎ ግንባር ለሚገኙ የሰራዊት አባላት የሰንጋ ስጦታ አበረከቱ። ==================
  September 15, 2021    News

በምስራቅ አማራ የሚገኙ የወሎ፣ የደብረ ብረሃን እና የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲዎች በወሎ ግንባር ለሚገኙ መከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ሀይል፣ ሚኒሻና ፋኖ 30 ሰንጋ በስጦታ አበርክተዋል። የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ባጋጠመው ተግዳሮት ምክንያት ድጋፍ ባያደርግም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ለጦር ሰራዊቱ ያለውን አጋርነት ገልጿል። ዩኒቨርሲቲዎችን ወክለው ንግግር ያደረጉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አጸዴ ተፈራ ወሎ ዩኒቨርሲቲ የጢጣን ቴርሸሪ ኬር ሆስፒታል ለደቡብና ማዕከላዊ እዝ መቀመጫ ከማመቻቸት ጀምሮ በግንባር ላይ ለሚገኙ የሰራዊት አባላት የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ አጋርነቱን እያሳየ እንደሆነ ገልጸዋል። አያይዘውም ፕሬዚዳንቷ ሶስቱ ዩንቨርሲቲዎች ለጦር ሰራዊቱ የዘመን መለወጫ ወሎ 10፣ ደብረ ብረሃን 10 እና መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ 10 በድምሩ 30 ሰንጋዎችን በስጦታ ማበርከታቸውን ተናግረዋል። የወሎ፣ የደብረ ብረሃንና የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲዎች የሰንጋ ስጦታ የተረከቡት የደቡብና የማዕከላዊ እዝ አመራሮች ዩኒቨርሲቲዎች እያደረጉ ላሉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በአጠቃላይ ሶስቱ ዩኒቨርሲቲዎች ያደረጉት የሰንጋ ስጦታ በገንዘብ ሲተመን ከ800 ሺ ብር በላይ ይሆናል።