ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሎጎና የአርዲቦ ሀይቆች ላይ የተከሰተውን የአሳ ዝርያዎች ሞት ላይ ጥናት አካሄደ።
  February 18, 2021    News

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሎጎና የአርዲቦ ሀይቆች ላይ የተከሰተውን የአሳ ዝርያዎች ሞት ላይ ጥናት አካሄደ። ሰሞኑን በደቡብ ወሎ ዞን በተሀለደሬ፣ በወረባቦና ቃሉ ወረዳዎች መካከል በሚገኙት የሎጎና የአርዲቦ ሀይቆች ላይ የተከሰተውን የብዝሀ-ህይወት ሞት ሞክንያት ለማወቅ የወሎ ዩኒቨርሲቲ በሀይቆች ላይ ጥናቶችን አካሄዷል። የወሎ ዩኒቨርሲቲ አዋሽና አባይ ተፋሰሶች የምርምር ተቋም እያካሄደ ባለው በዚሁ ጥናት በሀይቆች ላይ የተከሰተውን የብዝሀ-ህይወት ሞት መነሻ ምክንያት በከፊል ይፋ አድርጎል። የምርምር ተቋሙ አስተባባሪ ዶ/ር አሰፋ ተሰማ በሎጎና አርዶቦ ሀይቆች የተከሰተው የብዝሀ-ህይወት ሞት በሀይቆች ያለው የኦክስጅን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ ነው ይላሉ። ይህም የሆነው አሉ ዶ/ር አሰፋ የሀይቁ ውሃ በተፈጥሯዊ ሁኔታ ባጋጠሙት ተግዳሮች የውሃው ንብርብሮች (layers) በመደባለቅ የውሃው የኦክስጅን መጠን ወደ 1ሚሊ ግራም/ሊትር ወርዷል ሲሉ ገልጸዋል። እንደአስተባባሪው ገለጻ በሀይቁ ውስጥ የሚኖሩ ብዝሀ-ህይወቶች (በተለይም አሳዎች) በውሃው ውስጥ በህይወት ለመቆየት ከ4 ሚሊ ግራም/ሊትር በላይ የኦክስጅን መጠን ያስፈልጋቸዋል። በሁለቱም ሀይቆች ላይ በተካሄደው ምርምር በውሃው ውስጥ ያለው የኦክስጅን መጠን ከ1ሚሊ ግራም/ሊትር በታች ወርዶ በመገኘቱ የአሳዎች ሞት በሁሉቱም ሀይቆች እንደተከሰተ የማዕከሉ አስተባባሪ የገለጹት። በተለይም የሎጎ ሀይቅ ካለው ጥልቀት አኳያ ከፍተኛ የጉዳት መጠን ማስተናገዱን ነው ዶ/ር አሰፋ የገለጹት። አያይዘውም ዶ/ር አሰፋ ተሰማ የነሙና ጥናት በቤተ ሙከራ ተወስዶ እየተሰራ በመሆኑ ዝርዝር መረጃውን የላቦራቶሪ ውጤት እንደደረሰ ይፋ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።